Logo
FastMereja
ዓለም አቀፍ የሰዎች አዘዋዋሪ ይትባረክ ዳዊት (ክብሮም) በቁጥጥር ስር ዋለ

​#fastmereja I የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ያዘዋወረውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲፈለግ የነበረው አደገኛ ወንጀለኛ ይትባረክ ዳዊት (ክብሮም) ከ9 ግብረ-አበሮቹ ጋር መያዙን አስታወቀ። ተጠርጣሪው በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ውስጥ በድብቅ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር የዋለው፣ ፖሊስ ከዓለም አቀፉ የ"ROCK" ተቋም ጋር ባደረገው የጋራ ክትትልና የመረጃ ልውውጥ ነው።

​ተጠርጣሪው ይትባረክ ዳዊት በተለያዩ አገራት አድሀኖም፣ አህመድ፣ ሙኒር እና ክብሮም የሚሉ ስድስት የሀሰት ስሞችንና ፓስፖርቶችን በመጠቀም ለዓመታት ሲያመልጥ ቆይቷል። በምርመራው እንደተረጋገጠው፣ ግለሰቡና ቡድኑ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ወጣቶችን በመመልመል ሊቢያ ውስጥ በሚገኙ አምስት መጋዘኖች አግተው ኢ-ሰብአዊ ስቃይ ሲያደርሱባቸው ነበር።

​በዚህ የወንጀል ድርጊት ሳቢያ፦

​ከ100 በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።

​ከ50 በላይ ሴቶች ተደፍረዋል።

​ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ ተንቀሳቅሷል።

​ፌደራል ፖሊስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በ9 አገራት የሚገኙ 16 ተጎጂዎችን ጨምሮ የ100 ሰዎችን ምስክርነት ተቀብሏል። ተጠርጣሪዎቹ በወንጀል ያፈሩት ሀብትና የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ የተደረገ ሲሆን፣ የፖሊስ ምርመራ ተጠናቆ መዝገቡ ለዓቃቤ ሕግ መላኩ ተረጋግጧል።

​መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.