Logo
FIDEL POST NEWS
ጂጂ ዩቶጵያ በሚለው ዘፈኗ ጊዜያችን ሳያልቅ "ልዕለ-ሰው" እንድንሆን ትመክረናለች!!

👉 እውነትን ከውሸት ለይቶ ለትውልዱ መንገር አስቸጋሪ እንደሆነም ታስረዳለች

ዘፈንን ለሰላም ፣ለሀገር ፍቅር እና ለሰው ፍቅር ካዋሉ ኢትዮጵያዊ አቀንቃኞቻችን መሀል እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ ) ትጠቀሳለች።

የዘፈኑ ርዕስ ከግሪክ ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም በፖለቲካ፣ በህግ እና በማህበራዊ ኑሮ ረገድ ምንም ዓይነት እንከን የሌለበት፣ ሰላምና እኩልነት የሰፈነበት ምናባዊ ዓለም የሰፈነበት ፍጹም የሆነ ማህበረሰብ ማለት ነው።

ትልቁ ጥያቄ ግን በሰው ልጅ ፀብ አጫሪነት እና ስግብግብ ባህሪ እንደዚህ ዓይነት ማህብረሰብ መፍጠር ይቻላል ወይ የሚለው ነው?

ግጥሙ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ለአለም የሚተርፍ ፍቅርን ይሰብካል።ዩቶጵያ የምትገኘው በደመና ላይ ሳይሆን፣ "በልብ ውስጥ" እና "በእውነት መሰረት" ላይ በመመስረት ነው ይለናል።

ጂጂ "አንድነትን የሰው ልጅ መዋደድ" በማለት ሰላም የሚገኘው በፖለቲካ ስምምነት ሳይሆን በሰው ልጅ የልብ መለወጥ ነው ትለናለች። ሰው ልቡ ካልተለወጠ ፖለቲካው ቢለዋወጥም ሰላም እንደማይመጣ በመንገር ሰላም በግዳጅ ሳይሆን በፍቅር እንደሚመጣ በመንገር ስለ አንድነት ትሰብካለች።

ጂጂ "ሰው አይርሳ የሰላምን መንገድ" ስትል የተለመደ ምክር እየመከረችን ሳይሆን ፍጹም የሆነ ትዕዛዝ እያዘዘችን ነው። ሰላም ለሰው ልጅ አማራጭ ሳይሆን የሰውነት መገለጫ ግዴታ መሆኑን ትናገራለች።

"መሰረቱን ያጽናልን በእውነት" ስትል ጂጂ ለ"እውነት" የሰጠችውን ከፍተኛ ቦታ ያሳያል። ውሸት ባለበት ሰላም ሊኖር አይችልም፤ ሰላም በእውነት ላይ ካልተመሰረተ "የመቃብር ሰላም" እንደሆነም ዘፈኑ ያስረዳል።

​ጂጂ "Sing, sing, children of the world" በማለት የአለም ልጆች ሰላም ለጠማት አለም ስለ ሰላም እንዲዘፍኑ ትጠይቃለች።

ጂጂ "I believe we can survive in Uthopia" በማለት የሰው ልጅ ካለበት መከራ ወጥቶ ወደ ተሻለ ዓለም ሲሸጋገር ለማየት እንደናፈቀች እናያለን።

"ኢትዮጵያ"ን እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ ቀዳማይ ምስል ጂጂ ስላታለች። ኢትዮጵያ በግጥሙ ውስጥ "የደስታችን ቤት" በማለት ዜጎች ወደ እናታቸው ቤት ወደ ሰላማዊው መሠረታቸው የመመለስ ፍላጎታቸውን ታንፀባርቃለች።

ግጥሙ "አንድነትን የሰው ልጅ መዋደድ" ግለሰባዊ ፍላጎት ወደ ማህበራዊ አንድነት፣ ማህበራዊ አንድነት ደግሞ ወደ አለም አቀፋዊ ፍቅር የሚያድግበትን " ሂደት ያሳያል።

ዩቶጵያ ማለት ለጂጂ የሰው ልጅ ግጭቶችን ጨርሶ፣ እውነትና ነፃነት ተዋህደው የሚኖሩበት የታሪክ ፍፃሜ ነው። ግጥሙ ተስፋን መሰረት በማድረግ፣ መንፈስ ሁሌም ወደ ተሻለ ብርሃን እንደሚገሰግስ የሚያሳይ የጂጂ ፍልስፍና ነጸብራቅ ነው።

ጂጂ What’s the truth and what are lies በማለት እወነትና ውሸትን ለይቶ ለትውልድ ማስረዳት ከባድ እንደሆነ ትነግረናለች። እዚጋ ለጂጂ እውነት"ጭምብል" ናት። ጂጂ "Signal spake between the stations" በማለት የሰው ልጅ በመገናኛ ብዙሃን እና በሃሰት መረጃዎች መካከል ያለውን ግራ መጋባት ትገልፃለች።

ጂጂ "ፍቅራችን ነው መዋደድ አይጥፋ" በሚለው ጥሪዋ ሰላም የሰው ልጅ በራሱ ፍቃድ የሚፈጥረው እሴት እንደሆነ ትናገራለች ።

A hundred years from now / Who'll be left to stay" የሚለው የግጥሙ ክፍል የሰው ልጅ ሟች መሆኑን ሲረዳ ነው ህይወቱን በትክክለኛ መንገድ መምራት እንደሚጀምር ይሰብካል።

ግጥሙ "ጊዜ ለዘላለም አይቆይም" በማለት የሰላምን መንገድ አሁኑኑ እንድንይዝ መገፋፋቱ ህልውናዊ ጥሪ ነው።

"ልጅ ተወልዶ ወተትም ይጠጣ" የሚለው መስመር ሰላም ማለት ረቂቅ ቃላት ሳይሆኑ፣ አንድ ህጻን ወተት የሚጠጣበት፣ ምድር ፍሬዋን የምትሰጥበት "መኖር" እንደሆነ እንረዳለን።

ባጠቃላይ ይህ ዘፈን በልባችን ውስጥ ያለውን ብርሃን ተከትለን በመጓዝ ከግለሰብ አልፎ ለአለም የሚተርፍ ሰላም ማምጣት እንደምንችል ይሰብካል።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.