Logo
Getu Temesgen
አቶ አብነት ገ/መስቀል ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሬዝዳንት ሀላፊነት መልቀቃቸውን አሳወቁ

📌ተከታዩን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለ፦ ለተከበራችሁ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የቦርድ አባላት፣ ውድ ደጋፊዎች እና የክለቡ ቤተሰቦች

ጉዳዩ፦ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብን ለማዳን የተወሰነውን እርምጃ ስለመደገፍ

ክቡራትና ክቡራን፤
#ethiopia | እኔ አብነት ገብረመስቀል ኦዳ፣ ይህንን ታሪካዊ ክለብ በአጠቃላይ ላለፉት 24 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ፤ ከዚ ቀደም ብሎም ለ8 ዓመታት ክለቡን የማገልገል ታላቅ ዕድል በማግኘቴ የተሰማኝን ጥልቅ ኩራትና ምስጋና እየገለጽኩ ፤ ዛሬ በወሰንኩት ታሪካዊና ከባድ ውሳኔ ዙሪያ የሚከተለውን መግለጫ አቀርባለሁ።

ይህ ደብዳቤ ከፕሬዝዳንትነት ኃላፊነቴ መልቀቄን ለማሳወቅ ደብዳቤ ጽፌ ከጨረስኩ በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ፣ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ሃይለ እየሱስ፣ እና የአዲስ አበባ ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ባደረጉተ ስብሰባ ላይ ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቦርድ አባላት እና ደጋፊዎችን ያካተተ ስብሰባ በማድረግ ይህ ታሪካዊ ክለብ ለሁሉም ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የሚያሳይ ጉልህ ምልክት ነው። ይህ ዓይነቱ ትኩረት እና ተሳትፎ ክለቡን ሊያድን የሚችለው ትክክለኛ መንገድ መሆኑንም በጽኑ አምናለሁ።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ፣ በተለይም ከ1994 ዓ.ም. ፣ እኔ ወደ ፕሬዝዳንትነት ከመጣሁ ጀምሮ የተሰሩ ስራዎች እና የተገኙ አመርቂ ውጤቶች ዋና ዋናዎቹ እድሚቀጥለው ይገለፃሉ፦ ቡድናችን 15 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን በማንሳት ፣ 7 የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫዎችን በማንሳት ፣ 9 የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን በማንሳት ፣ ከ7 በላይ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫዎችን በማንሳት ፣ በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ውድድር አንድ የብር እና አንድ የነሃሰ ሜዳልያ ያገኘ ሲሆነ ፣ በ2009 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ውስጥ የገባ ብቸኛ ቡድን ነው። የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ከሀገር ዉስጥ እና ከዉጪ ሃገር የተጨዋቾች ግዢ የጀመረ ፣ በደረት ላይ ለሚደረግ ማስታወቂያ ክፍያ ያስጀመረ፣ ከተለያዩ የአዉሮፓ ሃገሮች የታወቁ አሰልጣኞችን በማስመጣት የአንበሳዉን ድርሻ የያዘ ነዉ። ለብዙ ተጨዋቾች ከፍተኛ ደሞዝ በመክፈል ህይወታቸዉ እዲቀየር ያደረገ ክለብ ነዉ ፣ በህክምናም ቢሆን ለራሳችንም ሆነ ለሌላ ቡድን ተጨዋቾች ያቅሜን ያህል ሳልቆጥብ ጥሩ ህክምና እንዲያገኙ በሀገር ዉስጥ እና በዉጪ ሃገር በአቅሜ ረድቻለሁ። በጠቅላላ በነዚ ውጤቶች በሃገሪቱ እግር ኳስ ውስጥ ወደር የሌለው የበላይነት እንዲኖረው መድከማችንን ያሳያል። የክለቡን መዋቅር ወደ አክሲዮን ማህበር በመቀየር 244 ሚሊዮን ብር የካፒታል ግብ እንዲኖረው በማድረግ፣ ክለቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር መሰረት ቢጣልም ተፈፃሚነት እዳያገኝ በውስጥ እንቅፋት የተቋረጠ ሲሆን በሌላ በኩል ደገሞ ፣ በቢሾፍቱ ከተማ በ24 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ አካዳሚ በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስም በመገንባት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ክለብ ያደርገዋል። እንዲሁም በለሚ ኩራ ከአዲስ አበባ መስተዳደር 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለዋናው ቡድን ለመለማመጃና ለመኖሪያ የተሰጠን መሆኑን በደስታ እየገለፅኩ ፣ በዚህም አጋጣሚ የአዲስ አበባ ከንቲባን ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ ላደረጉልን ሁሉ ድጋፍ ከልብ አመሰግናለሁ። ታዲያ እነዚ ሁሉ ሃቆች የዚሁ የዘመናዊነት ጉዞ አካላት ነበሩ።

ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ወቅት ክለባችን በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ከፍተኛ የፋይናንስ እና የአመራር ፈተና ውስጥ እንደሚገኝ ግልጽ ነው። ከደጋፊው ጋር በነበረን ጥልቅ ፍቅር እና መተሳሰብ ብዙ ርቀት ብንጓዝም፣ አሁን የሚታዩት ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች ክለቡን ለከፋ አደጋ እንዳያጋልጡት ስጋት አለኝ። በተለይም ከፋይናንስ ድጋፍ መቋረጥ ጋር ተያይዞ የመጡት ጫናዎች፣ የስታዲየም ግንባታ መቋረጥ እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ክለቡን ዋጋ እያስከፈሉት ይገኛሉ።

ለብዙ ዓመታት ድጋፋቸዉ ያልተለየን ከክለባችን ታሪክ ጋራ ተያያዥነት ያለዉ የቢጂአይ ኢትዮጰያ እንዲሁም ሚድሮክ ኢትዮጵያ እና የሚድሮክ እህት ኩባንያዎች ፣ በተለያየ ወቅት ደግሞ ቤቲንግ ኩባንያዎች ፣ ጎፈሬ ትጥቅ አምራች ድርጅት ፣ የሃይላንድ ዉሃ እና ፀሃይ ባንክ ላደረጉልን ድጋፍ አመሰግናለሁ ። ከ6 ዓመታት ወዲህ ግን ቃል የገቡትን እና የገቡትን ዉል ባለመፈፀማቸዉ ክለቡ ላይ ከፍተኛ የፋይናንስ ተፅኖ ቢፈጥርም እኔ እሰከ ዛሬ ድረስ ከራሴ እና ከወዳጆቼ ጋር በመሆን ብዙዉን ወጪዎች ሸፍነን እዚህ አድርሰናል ለነሱም ከልቤ ምስጋና አቀርባለሁ።

ልዩ ምስጋና ከሚገባቸዉ ደግሞ አይበገሬዎቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ የጀርባ አጥንት እና እንደ ወርቅ የተፈተኑት ደጋፊዎች በሙሉ ፣ የቦርድ አመራር በሙሉ ፣ ለመላዉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን አሰልጣኞች ፣ ተጨዋቾች ፣ የቀድሞ ተጨዋቾች ፣ የቡድን መሪዎች ፣ የህክምና ባለሙያዎች ፣ የፅፈት ቤት ሰራተኞች በሙሉ ፣ ለሹፌሮች ፣ ሜዳዎቹን ለሚንከባከቡት ሰራተኞች፣ በአካዳሚ ዉስጥ አገልግሎት ለሚሰጡት አባላት በሙሉ ፣ በየግጥሚያዉ ላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሚገኙ የፀጥታ አስተባባሪዎች ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ልሳን በጋዜጣና በሬዲዮ ልዩ ልዩ ዜናዎችና ፕሮግራሞችን ሲያቀርቡ ለነበሩት የሚዲያ አባላትን በሙሉ ፣ ለሸገር ሬዲዩ ጣቢያ ያለን ከፍተኛ አክብሮት ዘዉትር እሮብ ማታ የምንጊዜም ጊዮርጊስ የሚለዉን ፕሮግራም እንዳይቋረጥ ላደረጉልን ልዩ እገዛ ወ/ሮ መዓዛ ብሩ እና

አቶ አበበ ባልቻን በመላዉ የቅዱስ ጊዮርጊስ አባላት ስም ላመሰግን እወዳለሁ። እንዲሁም አቶ ሰለሞን በቀለ በስራአስኪያጅነት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከልቤ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። በመጨረሻም በአለም ዙሪያ ለምትገኙት ደጋፊዎቻችን ክለቡ በተቸገረበት ወቅት በሃሳብ እና በገንዘብ ላደረጋችሁልን ድጋፍ በጣም እናመሰግናለን።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፡ የእኔ ፣ የእናንተ እና የኛ ፣ የማይፋቅ ፣ የማይሸጥ እና የማይለወጥ ንብረታችን ነዉ።

ስለሆነም፣ ክለባችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከግለሰቦች ማንነት በላይ የሆነ ታሪካዊ ተቋም በመሆኑ፣ ይህ ተቋም ሊደርስበት ከሚችል ማንኛውም ጥፋት ለመታደግ እና ለክለቡ ሰላም ሲባል፣ አሁን እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ሙሉ በሙሉ ከመደገፌ ባለፈ በቅንነት የክለቡ ደጋፊ ብቻ ሆኜ ለመቀጠል መወሰኔን በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ አሳውቃለሁ። ውሳኔው ከቤተሰቦቼ ጋር በመመካከር የተደረገ ሲሆን፣ ዓላማውም እኔን ምክንያት በማድረግ በክለቡ ላይ የሚመጡ ጫናዎችን ለማርገብ ያለመ ነው።

ይህ አዲስ ምዕራፍ ለክለቡ የዕድሳት መነሻ ሊሆን ይገባዋል። ዛሬ የተጀመረው ውይይት ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው ሁሉም አካል ሃላፊነቱን በቅንነት እና ለታሪክ በሚያመች መልኩ ሲወጣ ነው። የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎቹ ምሰሶ እና ብርታቱ ናቸው ፤ ቦርዱ አስፈፃሚ ነው ፤ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ ሰጭ ነው ፤ ሁሉም ሲሰባሰብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም ያብባል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለአዲስ አበባ ስፖርት ቢሮ እና ትላንት ለተሰባሰቡ ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ።

ስለነበረን ጊዜያት እና ስለ መልካም ጊዜያችን ሁላችሁንም አመሰግናለሁ፡፡ቅዱስ ጊዮርጊስን ከልቤ እወደዋለሁ፡፡ሁሌም ስኬቱን ብቻ እመኛለሁ፡፡በርካታ የስኬት አመታት ከፊት ለፊታችን እንደሚጠብቀን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በታላቅ አክብሮት ፥ ሁላችሁንም እወዳችኋለሁ

አብነት ገብረመስቀል ኦዳ

ፕሬዝዳንት፣
ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ አንድ ክለብ አንድ ቤተሰብ !!

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ #balagerutv #atoabinet #gebremeskel

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.