Logo
FastMereja
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በዛሬው ዕለት 16 ባለስቲክ ሚሳዔል እና 119 ድሮን እንደተተኮሰባት ገለጸች

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ የኢራን ፕሬዝዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን ቀድመው በማያጠቁ ጎረቤት አገራት ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም በገለጹበት በዛሬው ዕለት የተተኮሱባትን 15 ባለስቲክ ሚሳዔሎች እና 119 ድሮኖች ማክሸፏን ገለጸች።

በሌላ በኩል በዱባይ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቅጥር ውስጥ በድሮን የተፈጸመ የሚመስል ጥቃትን የሚያሳይ ቪዲዮ ተሰራጭቷል።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ፤ የአየር መከላከያ ስርዓቱ 16 ባለስቲክ ሚሳዔሎችን እንደለየ እና ከዚያ ውስጥ 15 ያህሉ ተጠልፈው ባሕር ላይ መውደቃቸውን አስታውቋል።

ባለስቲክ ሚሳዔሎች በአብዛኛው በሮኬት የሚታገዙ የረጅም ርቀት መሣሪያዎች ሲሆኑ ለማምረትም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ይጠይቃሉ። ዝቅ ብለው የሚበርሩት ሰው አልባዎቹ ድሮኖች ደግሞ በጣም ባነሰ ዋጋ ይመረታሉ።

የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ባለው የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ዩናይትድ አረብ ኤምሬት ውስጥ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ሦስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 112 ሰዎች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ዛሬ በኤምሬትስ አየር መንገድ የተፈጸመውም የድሮን ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋገጠው ቪዲዮ አሳይቷል።

በአየር ማረፊያው ደቡባዊ ክፍል ከሚገኘው የማምረቻ ስፍራ የተቀረጸው ቪዲዮ፤ ከአየር ማረፊያው ተርሚናል ሕንጻ አቅራቢያ ተፈጠረን ፍንዳታ ያሳያል። ቪዲዮውን የቀረጸው ሰው “ሌላ ድሮን” በማለት ሲናገር ይሰማል።

ሰው አልባው በራሪ ከመጋጨቱ በፊት በድሮን ሞተር ከሚፈጠር ድምጽ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ድምጽ ይደመጣል። ፍንዳታው ከመፈጠሩ አስቀድሞ አንድ ቁስ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ታች ሲወርድ የሚታይ ቢሆንም ምን እንደሆነ ማረጋገጥ አልተቻለም።

ጥቃቱ በተፈጸመበት የአየር መንገዱ ስፍራ አቅራቢያ አራት አውሮፕላኖች እንደቆሙ ቪዲዮው ያሳያል።

ኤምሬትስ አየር መንገድ ዛሬ ጠዋት ሥራ እንዳቋረጠ የሚገልጽ መረጃ ካሰራጨ በኋላ አጥፍቶታል። ቀጥሎም እንደገና አገልግሎት መጀመሩን የሚገልጽ ልጥፍ አጋርቷል።

ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.