Logo
FIDEL POST NEWS
ዳሸን ባንክ በሸራተን አዲስ የኢፍጣር መርሃ ግብር አካሄደ

ዳሸን ባንክ የረመዳን ወር ምክንያት በማድረግ ለደንበኞቹ፣ ለሀይማኖት አባቶችና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች በሸራተን አዲስ ሆቴል ደማቅ የኢፍጣር መርሃ ግብር ዛሬ አከናውኗል።

ይህ መርሃ ግብር ባንኩ ካሉት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የ"ሸሪክ" (ከወለድ ነፃ) አገልግሎት ተጠቃሚዎች ጋር ያለውን ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከርና የአብሮነት እሴትን ለማጎልበት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

በዝግጅቱ ላይ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች እንደገለጹት፣ ዳሸን ባንክ የፋይናንስ ተቋም ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡ እሴትና እምነት ጠባቂ በመሆን አገልገሎቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ላይ ይገኛል።

​የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ዳሸን ባንክ የደንበኞቹን የፋይናንስ ፍላጎት ከሸሪዓ መርሆዎች ጋር በማጣጣም ረገድ ትልቅ ስኬት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ባለው ጽኑ አቋም፣ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ከደንበኞቹ በአደራ መልክ የሰበሰበውን ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለ131 አገር በቀል የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች መለገሱ የዚሁ ቁርጠኝነት አካል መሆኑን አብራርተዋል።

ይህ ልገሳ በተለይ ረመዳንን የመሰሉ የለጋስነት ወቅቶች ላይ ባንኩ ለማህበረሰቡ ደህንነት የሚሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀው ይህም በኢትዮጵያ የባንክ ታሪክ ውስጥ ተዘዋዋሪ ብድርንና የሰብአዊ ድጋፍን በማጣመር ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነው ብለዋል።

​በተለይ በሱማሌ ክልል ለሚገኙ ሴት ስራ ፈጣሪዎች የቀረበው የ100 ሚሊዮን ብር ከወለድ ነፃ ተዘዋዋሪ ብድር፣ ዳሸን ባንክ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማብቃት ያለውን ራዕይ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ በመርሃ ግብሩ ላይ ተጠቅሷል።

ይህ ተግባር ባንኩ ከትርፍ ባለፈ ለሀገር ግንባታና ለሴቶች ተጠቃሚነት የሚሰጠውን ስፍራ የሚያሳይ ሲሆን፣ የሸሪዓን መርህ ተከትሎ የሚሰጥ የፋይናንስ ድጋፍ እንዴት ማህበረሰባዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ማሳያ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።

ይህ የብድር አገልግሎት በክልሉ የሚገኙ ሴቶች የንግድ ስራዎቻቸውን እንዲያስፋፉና ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም በዝግጅቱ ላይ ተገልጿል።

​ዳሸን ባንክ እ.ኤ.አ በ2023 በባህሬን ማናማ በተካሄደው 9ኛው የኢስላሚክ ሪቴል ባንክ ሽልማት ላይ "The Strongest Islamic Retail Banking Window in Ethiopia" በሚል እውቅና ማግኘቱ ይታወሳል።
3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.