Logo
Getu Temesgen
ፈረሰኛውና ፈረሶቹ በጥቅሻ የሚግባቡበት ምድር‼️
🐎🐎🐎🐎🐎🐎🐎🐎🐎🐎🐎🐎🐎🐎
#ethiopia | ምድሩ ለፈረሶች ተመርጦ የተፈጠረ ይመስላል፤ ሕዝቡም ፈረስን ከሰማይ በአደራ የተቀበለ ደገኛ ሕዝብ ። የአገው ታሪክ በፈረስ ኮቴ በለምለም ምድር የተጻፈ በትውልድ የሚነበብ ሕያው ብራና ነው። 🐎🐎🐎

የአገው ታሪክ እንደ አምፖል ከጣራ በታች ሳይሆን እንደፀሐይ ከሰማይ በታች የሚያበራ ብርሃናማ የተጋድሎ ታሪክ ነው። አክሱም ሲነሳ ፈረሰኛው አገውና ፈረሶቹ በዚያ ይነሳሉ ።

ላሊበላም ሲዘከር ከነ ዛጉዌ ሥርወ መንግስታቸው ንጉስም ቅዱስም፤ ካህንም አናጺም፤ መሪም ዘካሪም ኾነው
ፈረስ ጋላቢዎቹ አገዎች፣ ከተጋላቢዎቹ ፈረሶቻቸው ጋር በወርቅ ቀለም ተጽፈው በዚያ አሉ።

የፓን አፍሪካኒዝም የልደት ምስክር ወረቀት አድዋ ሲነሳም ፈረሰኞቹ አገዎችና ፈረሶች፤ በአይበገሬነት ታሪካቸው በደማቁ ድላቸው በዚያ አሉ። በአድዋ ተራራ ከተቀበሩ እልፍ አርበኞች አጽም ጋር የፈረሶች አጽምም በዚያ አለ። ፈረሰኛውና ፈረሶቹ በየታሪኩ ምዕራፍ ለሀገር ግንባታ ጡብ ደርድረዋል፤ የስማቸውንም ሐውልት አቁመዋል ። 🐎🐎🐎

የፈረስን ውለታ አገው ያውቀዋል፤ እንኳን ለባለውለታው ፈረስ፤ ነፍስ ላለው ፍጥረት ሁሉ የሚራራው የአገው ሕዝብ፤ ፈረስን እንደ ልጁ መርጦ ይመግበዋል። በሥርዓትና በማዕረግ ያሳድገዋል፣ በትጋትና በሥልጣኔ ይገራዋል፣ በግርማና በሞገስ በተዋቡ አልባሳትና ጌጦች ይሸልመዋል። ፈረሱን በልኩ እንዲሠራ በሚገባውም እንዲያርፍ ያደርገዋል። 🐎🐎🐎

ፈረሱም ለአባቱ ለአገው ሕዝብ እንደሚታዘዘው ለሌላው የሚገራና የሚታዘዝ አይመስልም ። በእርሻው በኩል በግራም በቀኝም ተጠምዶ ትከሻው እስኪላጥ አርሶ፣ ወቅቶ፣ አዝመራ ተሸክሞ ወደ ጎተራ አስገብቶ አገልግሏል ። 🐎🐎🐎

አገው ልጁን ቢድር ሙሽሮቹን እንደሊሞዚን ተሸክሞ ጫጉላ አውጥቷል ። ቢታመም እንደ አምፑላንስ ኾኖ ሐኪም ደጅ አድርሷል ። ሞት መከራ ቢመጣ ከአልቃሽና አስለቃሽ ጋር ደክሞ፣ አልቅሶ በክብር ይሸኛል ። ዘመድ ቢናፍቁ ፈጣን ትራንስፖርት ኾኖ ወንዝ አሻግሮ ዘመድ በማገናኘት ናፍቆትን አስወጥቷል ። 🐎🐎🐎

አይሞሎ አይሞሎ ሞሎ ዎ!
ሲዋጋ ውሎ ሲዋጋ አመሸ፣
ጋሻውን በዘንግ እያንኮላሸ፡፡
ቦራ ብሎ ጠራው ጀግና ፈረሱን፣
እንኳን አግዜር ሰጠው የተመኘውን፡፡
የጀግናው ባለሟል እኔነኝ ፈረስ፣
ከተፋፋመው ጦር አብሬ ምደርስ፡፡
ጀግናው ፈረሰኛ መጣ ገሰገሰ፤
የጠላቱን ምሽግ እየደረመሰ። የተባለለት ...🐎🐎🐎

ጠላት ቢመጣ ጦር ሜዳ አድርሶ፣ ጠላትን እየረገጠ፣ በጌታው ፋንታ በጦሩም፣ በጎራዴውም፣ በጥይቱም እየቆሰለና እየሞተ ተዋግቷል ። ክብረ በዓላቱን ትርዒት እንደሰለጠነ ወታደር በሥርዓት ተሰልፈው ሰላምታ እየሰጡ ያደምቁታል። 🐎🐎🐎

ለዚህም በአገው ምድር ፈረስ፤ አርበኝነት፣ ነጻነት፣ ድል አድራጊነት፣ የሀገር ፍቅር እና አንድነት የሚንጸባረቅበት የድል ምልክት ኾኖ ይዘከራል ። ፈረሰኛው በንፁህ ባርኔጣ፣ በሎፊሳ፣ በነጭ ኮት እና ሱሪ (ግርቭ ታምባ) በገምባሌ እና አለንጋውን ከሰነደቁ ፤ ጋሻውን ከዘንጉ ጋር ይዞ ከመድመቁ በላይ፤ ፈረሱ በኮርቻ፣ በልቫቭ፣ በልጓም፣ በአምፓጉሲ እና በወደሊ ቀይ አበባ ይደምቃል፡፡ 🐎🐎🐎

የፈረሱ ሰላምታ አሰጣጥ፣ የድንግል ዓሳ ትርዒት፣ የስግሪያ፣ የጉግስ ፣ እና ሽርጥ ትርዒት ሲካሄድ ማየት ልብን ቀጥ የሚያደርግ ደስታ ይሰጣል። ፈረሰኛውና ፈረሱ በጥቅሻ የሚግባቡበት፣ የፈረስ ማዕበል በቀይ ጌጥ ተውቦ የሚፈስበት ትርዒት በአገው ምድር ሰማይ ሥር ይታያል። 🐎🐎🐎

ለሕጻናት ፈረሰኞች የሚታዘዝ ፈረስ በዚያ አለ፤ ለዐይነ ሥውሩ የሚታዘዝ መንገድ መሪ ብቻ ሳይሆን ከዐይናማዎቹ ጋር ተወዳድሮ አሸናፊ ፈረስ በዚያ አለ። ሴት ፈረሰኞች የሳይንስን የዙረት ስሌት ሽረው እየተሽከረከሩ የሚጋልቡት ፈረስ፣ በምልክት ተረድቶ የሚሽከረከር ፈረስ በአገው ምድር ይታያል ። 🐎🐎🐎

በአገው ምድር ሰባቱ ወንድማማቾች «አንክሺ፣ ባንጂ፣ ዚጋሚ፣ አዚኒ፣ ኳኩሪ፣ ቻሪና ሚቲክሊ» እንደአንድ ልብ መካሪ እንድ ቃል ተናጋሪ ናቸው። ፈረስ 🐎 ልዩ ምልክታቸው ስልጣኔ መለያቸው ነው።

ፀሐዩ አይሰማም እንጅ ከተሰማህ ለፀሐዩ አዊት ድጋግ (የአገው ጥላ) አለ። ለሆድህ አትጨነቅ አብዚ፣ ጉዝጉዝ፣ በመልክ በመልኩ ከጠላው ከጠጁና ከብርዙ ጋር በበቃኝ ይቀርባል ። በአገው ምድር የምታየውን ዐይተህ ታደንቀዋለህ፣ እያሰብኸው ትደመማለህ እንጅ ለመጻፍ እንዴት ይቻላል ?

በዚያ ምድር የተገኘህ፣ ፈረሰኛውና ፈረሶቹ በጥቅሻ ሲግባቡ ያየህ፣ ከፈረሱ ጋር ተጫወት።
አይሞሎ አይሞሎ ሞሎ ዎ! 🐎🐎
የፈንዞ ጌታ፣ የጥሪኝ ጌታ የሻሾ ጌታ፤ 🐎🐎
ጀምር ጨዋታ በል ጋሻ ምታ ግጠም እስክስታ ።

👉62 ሺህ ፈረሰኞችና ፈረሶች ያሉት፣ 🐎🐎🐎
👉86 ዓመታትን በሦስት ዐለቃ እየተመራ ዛሬ ላይ የደረሰ፣
👉ባህልን፣ ታሪክን፣ ባለውለታን የሚዘክር፣
👉 የድል አድራጊነት ምልክትና አንድነትን የሚያጠናክር፣
‼️ የአገው ፈረሰኞች 🐎 ማኅበር ‼️👌
እንኳን አደረሳችሁ ‼️
እንኮዋን 86ንቲ አጋው ፌሬስቴኑ ባልስ ታምፅኾስ‼️
🐎🐎🐎 የሀብከ ብርሃኔ ጥላሁን 🐎🐎🐎

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.