Logo
FIDEL POST NEWS
የራባት ሌሊት፦ የደም ስር ትርታ

የነፋሱ ሹክሽክታ

​ጥር 6, 2018 ከምሽቱ 5:00 ሰአት ።ብዙ ኢትዮጵያዊ በእንቅልፍ ላይ ነው ።ሞሮኮ ላይ አንድ ከባድ የኳስ ግጥሚያ ጀምሯል።

የራባት ምሽት ብርዳማ ቢሆንም፣ በልዑል ሞውላይ አብደላህ ስታዲየም ውስጥ ያለው ድባብ ግን የጋለ እሳት ነበር። ስልሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ ስምንት ነፍሳት ስታዲየሙን ሞልተውታል። አየሩ በጭስ፣ በባንዲራዎች ሽውሽውታና በከበሮ ድምፅ ተሞልቷል።
​በመልበሻ ክፍል ውስጥ ዋሊድ ረግራጉ የቡድኑን አባላት ትኩር ብሎ ተመለከተ። በ2004 ተጫዋች ሆኖ የፍጻሜውን ዋንጫ ሲያጣ የተሰማው ቁስል ዛሬም በልቡ ውስጥ አለ። "ዛሬ ታሪክ ራሱን አይደግምም፣ ዛሬ ታሪክን አዲስ አድርገን እንጽፋለን" አላቸው።
​በሌላ በኩል የናይጄሪያው አሰልጣኝ ኤሪክ ሼል ከዋክብቱን—ቪክቶር ኦሲሜንን፣ ሉክማንንና ቹኩዌዜን—ይዞ የሞሮኮን ኩራት ለመስበር ቆርጦ ተነስቷል።

የ90 ደቂቃው ትግል

​ጨዋታው ሲጀመር የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ ልክ እንደ አስማተኛ ኳሷን እግሩ ስር አጣበቃት። እያንዳንዱ ንክኪው ስታዲየሙን ያስጮኻል። አሽራፍ ሀኪሚ ከመስመር ወደ መስመር እንደ መብረቅ ይመላለሳል። ሆኖም የናይጄሪያው ተከላካይ ካልቪን ባሴ እንደ ጥቁር ድንጋይ የማይናወጥ ግድግዳ ሆነባቸው።

​ናይጄሪያውያን ልክ እንደ አድብቶ እንደሚጠብቅ አንበሳ ነበሩ። ጥቂት ኳሶችን ብቻ ወደ ግብ ሞከሩ፣ ነገር ግን እያንዳንዷ ሙከራቸው የሞሮኮን ደጋፊዎች ልብ ትነቅላለች። ደቂቃዎቹ ሲከንፉ፣ በሜዳው ላይ ያለው ትግል ከእግር ኳስ አልፎ የጥንካሬና የጽናት ፈተና ሆነ። 90ኛው ደቂቃ ሲጠናቀቅ ሰሌዳው አሁንም 0-0 ይላል። ጭንቀቱ ነፍስ ያስጨንቃል። በዚህ ሰአት ስልክ ቢደወል ጆሮ ቀልብ ሰጥቶ መስማት አይችልም።

​ የሁለቱ ደቂቃዎች ቁማር

​ተጨማሪ 30 ደቂቃዎች። ተጫዋቾቹ በድካም እየተዝለፈለፉ ነው። ብራሂም ዲያዝ ኃይሉ አልቆበታል፣ ግን አሁንም ይሮጣል። የሞሮኮው ግብ ጠባቂ ያሲን ቡኑ ጓንቶቹን እያጠባበቀ ወደ ሰማይ ተመለከተ።
​118ኛው ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ ኤሪክ ሼል አለምን ያስገረመ ውሳኔ አስተላለፉ። የቡድኑን መሪና ድንቅ አጥቂ ቪክቶር ኦሲሜንን አስወጥተው ሳሙኤል ቹኩዌዜን አስገቡ። ስታዲየሙ በሹክሹክታ ተሞላ። "ኦሲሜን ሳይኖር መለያ ምት?" ይህ ውሳኔ ወይ የታሪክ ጀግና ያደርጋቸዋል፣ ወይም የውድቀታቸው መጀመሪያ ይሆናል።

​ የያሲን ቡኑ "ጥቁር አስማት"

​መለያ ምት ተጀመረ። ስታዲየሙ መቃብር ውስጥ ያለ ይመስል ፀጥ አለ። መርፌ ቢወድቅ ይሰማል።
​የናይጄሪያው ቹኩዌዜ... አሰልጣኙ ተስፋ ጥለውበት ያስገቡት ተጫዋች። ሮጦ መታ... ቡኑ እንደ ድመት ተወርውሮ ኳሷን አዳናት! ስታዲየሙ ሊፈርስ ደረሰ። የሞሮኮው ደጋፊዎች ድምፅ ራባትን አናወጣት።

​ቀጥሎ ብሩኖ ኦንዬማቺ መጣ። በቡኑ አይኖች ውስጥ ያለው መተማመን ተጫዋቹን ያስፈራው ይመስላል። ቡኑ በድጋሚ ኳሷን አዳናት! "ያሲን! ያሲን!" የሚለው ጩኸት ሰማዩን ቀደደው። በሞሮኮ በኩል አሽራፍ ሀኪሚ፣ ኒል ኤል አይናዊ እና ኤሊሴ ቤን ሰጊር ያለምንም ስህተት መረቡን አናወጡት።

​የታሪክ መደምደሚያ

​የመጨረሻው ምት። ዩሱፍ ኤን-ነስሪ ኳሷን ይዞ ቆሟል። ኳሷን ከመታ መላው ሞሮኮ ወደ ፍጻሜ ትገባለች። ካልመታ ግን ጭንቀቱ ይቀጥላል።
​ኤን-ነስሪ ኳሷን አያት... ስታዲየሙ ትንፋሹን ዋጠ። ሮጦ መታ! ኳሷና መረቡ ሲገናኙ፣ የራባት ሌሊት ወደ ደማቅ የብርሃንና የደስታ ውቅያኖስ ተለወጠች። ሞሮኮ 4-2 በሆነ ውጤት ናይጄሪያን አሸንፋ ለፍጻሜ አለፈች።

​ የሰሜን አፍሪካ ንጋት

​በዚህ ሌሊት ማንም አልተኛም። ከታንጂየር እስከ ካዛብላንካ፣ ከማራካሽ እስከ ፌዝ ህዝቡ ወደ አደባባይ ወጣ። መኪናዎች ጡሩምባ ያሰማሉ፣ እናቶች እልል ይላሉ። አየሩ በ "ዲማ ማግሬብ" መዝሙር ታጥቧል።

​በናይጄሪያ በኩል ግን ጸጥታ ነገሰ። የቀድሞ ተጫዋች ዋይዲ አካኒ በአሰልጣኙ ውሳኔ ተቆጥቶ "ዝግጅት አነስቶን ነበር" ሲል ለጋዜጠኞች ተናገረ። ኦሲሜን በመልበሻ ክፍል ውስጥ ተቀምጦ በሀዘን አንገቱን ደፍቷል።

​አሁን ጥር 10ይናፍቃል። የአትላስ አንበሶች ከሴኔጋሉ አንበሳ ሳዲዮ ማኔ ጋር ለዋንጫ ይፋጠጣሉ። የራባት ሌሊት የድል ሽታ እንደያዘች ወደ ንጋት ተሻገረች። ሞሮኮ ታሪክ ለመስራት የቀራት አንድ እርምጃ ብቻ ነው።
7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.