Logo
FIDEL POST NEWS
ከ1 ቢሊዮን ወደ 850 ሚሊዮን ዶላር፦ የኢትዮጵያ የዩሮ ቦንድ እዳ እንዲቀንስ ስምምነት ተደረሰ

​ኢትዮጵያ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ጋር ስታደርገው የነበረው የብድር ሽግሽግ ድርድር ስኬታማ ውጤት ማስመዝገቡ የተገለጸ ሲሆን፣ በመሰረታዊ ነጥቦች ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት የሀገሪቱ አጠቃላይ የዩሮ ቦንድ እዳ መጠን በ15 በመቶ ወይም በ150 ሚሊዮን ዶላር እንዲቀንስ ተደርጓል።

ዓለም አቀፍ ጠበቆችን ቀጥራ ከአበዳሪዎች ጋር ስትደራደር የቆየችው ኢትዮጵያ፣ የ1 ቢሊዮን ዶላር እዳ እንዲሸጋሸግላት ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን የድርድሩ ሰነድ የሚያሳይ ሲሆን ይህም ለሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ እመርታ ተደርጎ ተወስዷል።

​በስምምነቱ መሰረት ዋናው የብድር መጠን (Haircut) ተደርጎለት ወደ 850 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ እንዲል የተወሰነ ሲሆን፣ ይህ እዳ እስከ 2020 የኢትዮጵያ በጀት ዓመት ተከፍሎ እንዲጠናቀቅ ታቅዷል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል በሦስት ዙር መከፈል የነበረበትና ሳይከፈል በመቆየቱ ኢትዮጵያን ለ "ቴክኒካዊ ውድቀት" (Technical Default) ዳርጓት የነበረው የ99 ሚሊዮን ዶላር የወለድ እዳ፣ አሁን ላይ ሀገሪቱ በአንድ ጊዜ ለመክፈል መስማማቷ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

​የረጅም ጊዜ ክፍያውን በተመለከተ፣ በቀጣዮቹ 8 ዓመታት ውስጥ የተሻለ የወጪ ንግድ ገቢ ከተገኘ ከገቢው 2.5 በመቶ በመቀነስ በዓመት 180 ሚሊዮን ዶላር እንድትከፍል ተወስኗል።

ይህ አሃዝ አበዳሪዎች ቀደም ሲል ከጠየቁት የ4.75 በመቶ የክፍያ ምጣኔ በእጅጉ የቀነሰ ሲሆን፣ ይህም በIMF የኢኮኖሚ ግምገማዎች ላይ ተመስርቶ የቀረበ የክፍያ አማራጭ መሆኑ ታውቋል። ስምምነቱ በይፋ ሥራ ላይ እንዲውልም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት
(IMF) የመጨረሻ ይሁንታ እየተጠበቀ ይገኛል።

​ይህ የብድር ሽግሽግ ስምምነት ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ገበያ በድጋሚ ለመመለስ ለምታደርገው ጥረት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።

የእዳ ጫናው መቀነሱ እንደ Fitch እና S&P ያሉ ተቋማት ለሀገሪቱ የሚሰጡትን የክሬዲት ደረጃ ሊያሻሽለው እንደሚችል የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም በሀገሪቱ ላይ የነበረውን የብድር አለመክፈል ስጋት በመቀነስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) እንዲጨምር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራም የሚል ትንበያ ባለሙያዎች ይሰጣሉ።

​ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2014 የገባችበት የ1 ቢሊዮን ዶላር የዩሮ ቦንድ እዳ በታህሳስ 2023 መከፈል የነበረበት ቢሆንም፣ በወቅቱ በነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ሳይከፈል መቆየቱ ይታወሳል። ይህ አዲስ ስምምነት ሀገሪቱ ካለባት የብድር ጫና ወጥታ የጀመረችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ (Macroeconomic Reform) በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚረዳ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የድርድሩ ውጤት ያመለክታል።
7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.