Logo
Getu Temesgen
ህንድ እና ህንዳውያን:- የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጆች!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

"... የጥንታዊት ታሪክና ገናና ሥልጣኔ ባለቤት፤ የአፍሪካና የጥቁር ሕዝብ ታላቅ የነጻነት ተጋድሎ ምልክት ከሆነች አገር- ኢትዮጵያ ይሄ የክብር ኒሻን ስለተበረከተልኝ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው፤ በ1.4 ቢሊዮን በሚሆነው የአገሬ የህንድ ሕዝብ ስም ምስጋናዬን ለመግለጽ እወዳለሁኝ...፤"

በአገራችን ኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የህንዱ ጠቅላይ ሚ/ር ናኔድራ ሞዲ- በጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ኒሻን በተበረከተላቸው ጊዜ ከላይ በመግቢያዬ ላይ ከጠቀስኩት ንግግራቸው ባሻገር በንግግራቸው - ህንድና ህንዳውያን አገራችን ኢትዮጵያ በፋስሽት በተወረረች ወቅት ከጎናችን መቆማቸውን ታሪክ አጣቅስው ተናግረዋል።

ህንድ እና ህንዳውያን:- የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጆች!!

የቅኝ ገዥዎችን ቅስም ካነካከተውና መላው አውሮፓንና ነጮችን በድንጋጤ እጃቸውን በአፋቸው ላይ እንዲጭኑ ያደረጋቸውን፤ አንፀባራቂውን የዐድዋውን ድል- ለመበቀል ፋሽስት ኢጣልያ ከ40 ዓመታት ዝግጅት በኋላ በአየርና በምድር የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው ታጥቆና እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሕግ የተከለከለ የመርዝ ቦምብ ሳይቀር ተሽክሞ ነበር የመጣው።

"... ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያን በዓለም ፊት የሚኮሩበት ነጻነታችውና ሉዓላዊነታቸው በቅኝ ግዛት ቀምበር ስር እንዲወድቅና ኢትዮጵያውያን ዳግመኛ አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዳይሄዱ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ መቀጣጫ ሊሆኑ ይገባል!!" በሚል እብሪትና ትእቢት ፋስሽቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ የበቀልና የጭካኔ ሰይፉን በኢትዮጵያውያን ላይ መዘዘብን።

በዛ የመከራና የጭንቅ ዘመን ህንድና ህንዳውያን ከኢትዮጵያ ጋር ቆመዋል፤ በዓለም መድረክ ድምፅ ሆነውናል። ታሪክን ምስክር እናድርግ፤ በወቅቱ የህንድ ጠቅላይ ሚ/ር የነበሩት ጃኋራል ኔህሩ በህንድ ፓርላማ ባሰሙት ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፤

"We in India can do nothing to help our brethren in distress in Ethiopia… But we can at least send them sympathy… in the hour of their trial. We stand with them today in their sorrow…" (quoted in Indian government records and MEA speeches).

"... ምንም እንኳን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ለጊዜው ምንም ማድረግ ባንችልም- ለነጻነታቸው በሚያደርጉት ተጋድሎአቸው ከጎናቸው መሆናችን የሚገልጽ ልባዊ መልእክታችንን ልንልክላቸው እንወዳለን፤ በዓለም አቀፍ መድረክ ለኢትዮጵያውያን የፀረ-ፋሽስት እና የፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ የጋራ ድምፅ እንሆናቸዋለን...፤"

ኢትዮጵያ እና ህንድ በቀደመው ዘመን

ጥንታዊት፤ የገናና ታሪክና የግዙፍ የሥልጣኔ ባለቤት የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ- እንደ አገራችን ሁሉ የሺህ ዘመናት ታሪክና የሥልጣኔ ባለቤት ከሆነችው ህንድ ጋር ለ2000 ሺህ ዓመታት በፊት በህንድ ውቅያኖስ እና በቀይ ባሕር አማካኝነት የአፍሪካን ድንበር የተሻገረ የንግድ ግንኙነት/Martime Trade እንደነበረን የታሪክ ድርሳናት የአርኪዮሎጂ ሳይንስ ግኝቶች ይመሰክራሉ።

ወጌን ፈር ለማስያዝ ይረዳኝ ዘንድ ከታሪክ ድርሳናት በጥቂቱ ላጣቅስ፤

Neville Chittick, የተባለ ምሁር፤ "Indian Relations with East Africa before the Arrival of the Portuguese" በሚል በጻፈው መጽሐፍ በህንድ በኩሻን ሥርወ-መንግሥት ዘመን መገበያያ የነበሩ የወርቅ ሳንቲሞች በአርኪዮሎጂ ጥናት በአክሱምና በደብረዳሞ መገኘታቸውን ተጽፏል። ይኸው ምሁር፤ የህንድ የጉፕታ ዘመነ መንግሥት አሻራ የሆኑ ቁሳቁሶች፤ የከበሩ ጌጣጌጦችና ጨሌዎች በጥንታዊቷ አክሱም ከተማና የኢትዮጵያ ወደብ በሆነችው አዶሊስ መገኘቱን አትቷል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ/በአክሱም ታሪክና ሥልጣኔ ላይ የተጻፉ በርካታ የታሪክ ድርሳናትና የጉዞ ማስታወሻዎች እንደሚጠቁሙት፤ አክሱማውያን የዝሆን ጥርስ፣ ወርቅ፣ ዕንቁ፣ ሃርና የከበሩ ማዕድናትን... ወዘተ. በቀይ ባሕርና በህንድ ውቅያኖስ አማካኝነት ከህንድና ከመካከለኛው ምሥራቅ አጋራት ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር።

የግሪክ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መነኩሴና ተጓዥ የነበሩት አባ ኮስሞስ ኢንዲክሎፕተስ፤ "the Periplus of Eritrean Sea" በሚል አርእስት ከ 1500 ዓመታት ገደማ በፊት በጻፉት የጉዞ ማስታወሻቸው፤

"... ኢትዮጵያውያን/አክሱማውያን በጥንት ዘመን በቀይ ባሕር በኩል- ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከዐረቢያ፣ ከቻይና ከህንድ ጋር የጠበቀ የባሕር ላይ የንግድ ግንኙነት እንደነበርን፤" ጽፈዋል።

እንደ ማጠቃለያ፤

የህንድና የኢትዮጵያ ግንኙነት ሺሕ ዘመንን የተሻገረ ጠንካራ የታሪክና የሥልጣኔን እሤቶችን የሚጋራ ነው። በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያና የህንድ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ጠንካራ መሠረትን ይዞ ተጀመረ። በደርግም ሆነ በዘመነ ኢሕአዴግ መንግሥታት ቢቀያየሩም የሁለቱ አገራት ግንኙነት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።

ኢትዮጵያና ህንድ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ... ወዘተ. ረገድ የጠበቀ ትስስር አላቸው። በዓለም ዙሪያ በሰላም ማስከበር ዘመቻ ሁለቱ አገራት- ኢትዮጵያና ህንድ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ አገራት ናቸው። በብሪክስ አገራትና በደቡብ ደቡብ ትብብር መድረክ ህንድና ኢትዮጵያ የጎላ ሚናን እየተጫወቱ የሚገኙ ሀገራት ናቸው።

የዛሬውን ኢትዮጵያንና ህንድን የተመለከተውን ወጌን- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር/ፕሮፌሰር፤ በአንድ ወቅትም በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር ዶ/ር ትዝታ ሙሉጌታ አባባል ለመቋጨት ወደድኹ፤

"የኢትዮጵያና የህንድ ግንኙነት በማይናወጽ ጠንካራ የታሪክ መሠረትና የእርስበርስ ትብብር ላይ የቆመ ነው፤"

የኢትዮጵያና የህንድ ግንኙነት ይለምልም!!

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.