Logo
Getu Temesgen
የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን በአህጉር አቀፍ ደረጃ እውቅና ተሰጠው
#ethiopia | የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ለአህጉር አቀፉ የአፍሪካ የባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን (African traditional sports and games confederation) ያቀረበው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ በዛሬው ዕለት በዙምባብዌ ሀራሬ እየተካሄደ በሚገኘው የኮንፌዴሬሽኑ አመታዊ የባለድርሻ አካላት ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እውቅና ተሰጥቶታል።

በ1977 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን የኢትዮጵያዊያን ልዩ መለያ የሆኑ ባህላዊ ስፖርቶች እና ጨዋታዎች በጥናት እና ምርመር በመታገዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲተላለፉ የማልማት፣ የማሳደግ፣ የመጠበቅ እና የማስተዋወቅ ስራዎችን በስፋት እየሠራ ይገኛል።

ፌዴሬሽኑ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽኖች ቀድሞ ከረዥም አመታት በፊት የተመሠረተ እና በርካታ ስራዎች የሰራ በመሆኑ ለተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ሠፊ ተሞክሮ አቅርቧል።

በተጨማሪም አብዛኛው የኮንፌዴሬሽኑ አባል ሀገራት የባህል ስፖርት ፌዴሬሽኖች ከተመሠረቱ አጭር ጊዜ የሆናቸው እና ገና በህግ እና በመመሪያዎች ያልተጠናከሩ በመሆናቸው በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የልምድ ልውውጦችን ማድረግ እንደሚፈልጉ ተገልጿል።

አመታዊ የባለድርሻ አካላት ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ህይወት መሀመድ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ፌዴሬሽኑ እውቅናን በማግኘቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው በብዝሃነት ያሸበረቀች አፍሪካን ለመፍጠር በሁሉም ሀገራት ውስጥ የሚገኙ አንጡራ ባህሎች እና እሴቶች ጉልህ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

አክለውም ፌዴሬሽኑ የአፍሪካ የባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን አባል በመሆኑ ከሌሎች ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጦችን በማድረግ በቀጣይ በአህጉር እና በአለም አቀፍ ደረጃ ለመስራት የታቀዱ በርካታ ስራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመስራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

አመታዊ የባለድርሻ አካላት ጉባዔው ነገም ይካሄዳል።

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.