Logo
Getu Temesgen
ቤማንዳ ሶልዩሽንስ በአዲስ አበባ ቢሮ ሥራ ጀመረ
#ethiopia | በሀገረ አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀበሻ ማኅበረሰብ አባላትን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት አስልጥኖ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ተቀጥረው ራሳቸውን፣ቤተሰባቸውን እና ሃገራቸውን እንዲረዱ ያደረገው ቤማንዳ ቴክ በኢትዮጵያ እህት ኩባንያ የሆነውን ቤማንዳ ሶልዩሽንስ በይፋ ሥራ መጀመሩን እና ቢሮ መክፈቱን አስታወቀ።

መስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም አ.አ ኢትዮጵያ
ቤማንዳ ሶልዩሽንስ ላለፉት 13 ዓመታት በአሜሪካ የICT ስልጠናዎችን ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ከ3000 በላይ ኢትዮጵያዊያንን አስተምሮ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ያስቻለ ተቋም ነው፡፡

አሁን ላይ ደግሞ በሀገረ አሜሪካ ያካበተውን ልምድ በመያዝ እህት ኩባንያ የሆነውን ቤማንዳ ሶልዩሽንስ በኢትዮጵያ ተገቢ የሆነውን ፈቃድ በመውሰድ በይፋ ሥራ መጀመሩን በቢሮ መክፈቻ መርሐ ግብር አስታወቀ።

ቤማንዳ ሶልሽንስ መስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም የፌደራል፣ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፣ የፋይናንስ ተቋማት ባለቤቶች እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የከፍተኛ ትምህርት ተወካዮችና ተመራማሪዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የንግድ ድርጅቶች ወኪሎችና በተለያዩ የሥራ መስኮች ታዋቂ የሆኑ ከ100 በላይ ታጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ቢሮ በመክፈት በይፋ ሥራ መጀመሩን በግራንድ ኤልያና ሆቴል በተካሄደ ደማቅ የቢሮ መክፈቻ መርሐ ግብር አብስሯል፡፡

ተቋሙ የተለያዩ የማይክሮሶፍት እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት ያላቸው አጫጭር የICT ስልጠናዎችን ከመስጠት ባሻገር ማናቸውንም ተቋማት ዘመኑ በሚጠይቀው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ራሳቸውን እንዲያዘምኑ ማለትም ወጪ የሚቀንሱበት፣ትርፋማነት የሚጨምሩበት፣ የሠራተኞቻቸው ውጤታማነት የሚያሳድጉባቸው መንገዶች እንዲዘረጉ በሙያው የማማከር አገልግሎትም ጭምር የሚሰጥ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አቶ ወሰን ተክለማርያም ተናግረዋል።

ለአራት ወራት ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ የሚሰጠው ስልጠና በኢትዮጵያ 2ኛ ዙር ምዝገባ ማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን የቤማንዳ ሶልዩሽንስ መስራቾችና ባለቤቶች በመስኩ ያላቸውን እውቀትና ልምድ ይዘው በመምጣት የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ የማገዝ ራዕይ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ተቋሙ ይዞት የመጣው ዕድል ሰልጣኞች ዕውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱ ከማገዙም ባለፈ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸው ነው ብለዋል፡፡ በዚህም በማንኛውም የሥራ ዘርፍም ሆነ የትምህርት መስክ ያለ ሰው ስልጠናውን መውሰድ እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

የቤማዳ ሶልዩሽንስ እናት ድርጅት ቤማንዳ ቴክኖሎጂ መስራችና ፕሬዚዳንት ዓለማየሁ ንዳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው እና ተወዳዳሪ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ይዞ መምጣት ኢትዮጵያ ለወጠነችው የዲጂታል ሽግግር ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአሜሪካ ለዓመታት ውጤታማ የሆኑበትን ዘርፍ ልምድ ኢትዮጵያዊያን ብሎም አፍሪካዊያን ወጣቶችን ለማብቃት የሚያግዝ እግረመንገድ ደግሞ የኢትዮጵ መንግሥት አይሲቲን (ICT) ከአምስቱ የኢኮኖሚ መሰረቶች አንዱ አድርጎ የያዘውን ስልታዊ ዕቅድ ከግብ እንዲደርስ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህ ይፋዊ የሥራ መጀመር እና ቢሮ መክፈት መርሐ ግብር ተጋባዥ ምሁራን የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡ ሲሆን በተለይ በፕሮፌሰር አበባው ይርጋ የዲጂታላይዜሽን አስፈላጊነት እና ኢትዮጵያዊያን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስልጠናዎች ወስደው ራሳቸው በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ የሥራ ገበያ ተወዳዳሪ ከማድረግ አንጻር እንደ ቤማንዳ ያሉ ተቋማት የሚኖራቸው የጎላ ሚና ከመቼው ጨረሱ በሚያስብል መልኩ ጣፋጭ አድርገው በአጭሩ አቅርበዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ለICT ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱንና ዘመኑም ይህን የሚፈልግ እንደመሆኑ መጠን ቤማንዳ ሶልዩሽንስ የኢትዮጵያን የዲጂታላይዜሽን ሽግግር በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ ወጣቶች ስልጠና በማግኘት የትም መሄድ ሳያስፈልጋቸው እዚሁ ተቀምጠው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተቀጥረው የመሥራት ዕድልን የሚያስገኝላቸው መሆኑን ተጠቁሟል፡፡

በቦታው የተገኙ የተለያዩ የፋይናንስና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተቋሙ ይዞት ያመጣውን የስልጠና እና የማማከር አገልግሎት ለሥራቸው ውጤታማነት እንደሚያግዝ በመግለፅ ወደፊት አብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ቤማንዳ ሶልዩሽን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ካመጣቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል አንዱ የትምህርት አስተዳደር ሥርዓት (Learning management System) ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙት ዶ/ር ሶስና መንግስቱ የትምህርት አስተዳደር ሥርዓት (LMS) የበይነ-መረብ ሰልጠናን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማበረታታት ካለው ተነሳሽነት እና ፍላጎት አንጻር ሊያበርከት የሚችለው ፋይዳ ዳሰሳቸውን አቅርበዋል ።

እንዲሁም ሌሎች ከቤማንዳ ሶልዩሽንስ ስልጠና እና የማማከር አገልግሎት ጋር ተያያዥነት ያላቸው አስተያየቶች እና ዳሰሳዎች በሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሰናድቶ የቀረበ ሲሆን የንብ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሺሰማ ሸዋነካ ስለ ቤማንዳ አስፈላጊነት ለተሳታፊዎቹ ገለፃ አድርገዋል።

የቤማንዳ ሶልዩሽንስ መስራች እና ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ አለማየሁን ንዳ መመለስ በሚል ርዕስ ከዛሬ 17 ዓመታት በፊት ለድህረ ምረቃት ትምህርታቸው ወደ አሜሪካ ሲሄዱ ትምህርታቸውን አጠናቀው በተማሩት ትምህርት ወደ ሀገርቸው ለመመለስ አቅደው የነበረ ቢሆነም የሥራ እና የትምህርት ዘርፋቸውን ቀይረው ከራሳቸው አልፈው ለብዙዎች የዕውቀት እና የሥራ መንገድ ከፍተው ከ17 ዓመታት በኋላ ለሃገር እና ለትውልድ ጠቃሚ የሆነን የቴክኖሎጂ ዕውቀት ለማሸጋገር ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ህልማቸው ለታዳሚ እጅን አፍ ላይ በሚያስጭን መልኩ አቅርበዋል።

አቶ አለማየሁን ንዳ ባለፉት 13 ዓመታት በአሜሪካ ካስተማሯቸው 3000 በላይ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መካከል ከ2000 በላዮቹ በአሜሪካን ሀገር በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች በፌደራል እንዲሁም በስቴት መንግሥታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በከፍተኛ ደሞዝ ተቀጥረው ራሳቸውን፣ቤተሰባቸውን እና ሀገራቸውን መጥቀም መቻላቸውንም አስረድተዋል።እንደእሳቸው ሁሉ በተለያዩ መስኮች እውቀት እና ገንዘብ ያላቸው ዲያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተለይም ወጣቱን ትውልድ ተጠቃሚ በሚያደርጉ የሥራ መስኮች ላይ እንዲሠማሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ሚካኤል አስራት የቤማንዳ ሶልሽንስ ሌላኛዉ መስራች እና ባለቤት ገለፃ እንዳደረጉት ቤማንዳ ቴክኖሎጂ የICT ስልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ ተቋማትን የማማከር አገልግሎት በመስጠት ይታወቃል፡፡ ምስረታውን ባደረገበት አሜሪካ ከስልጠናው ባሻገር በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የማማከር አገልግሎት ረገድ መልካም ዝናን ያተረፈ እና በርካታ ደንበኞችን ያፈራ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ሚካኤል አስራት አያይዘውም ቤማንዳ ሶልዩሽንስ በአምስት ዋና፣ዋና ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረጉ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ተቋም ነው ብለዋል።

እነዚህም፡-
ስልጠና፡ ቤማንዳ ሶልዩሽንስ ከማማከር አገልግሎት ባሻገር በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ስልጠና ዘርፍ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ተቋም ሲሆን ቤማንዳ እስከአሁን ለገበያ ምቹ እና ውጤት ተኮር ክህሎቶች ላይ በማተኮር ከ3,000 በላይ ሰዎችን አሰልጥኗል።

ከእነዚህ ውስጥ ከ2,000 በላይ የሚሆኑት በፌዴራል ተቋማት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በግል ኩባንያዎች ውስጥ ሥራ አግኝተዋል። ይህም የሥልጠናውን ጥራት ብቻ ሳይሆን ከሥራ ገበያው ፍላጎት ጋር የተጣጣመ መሆኑን ያሳያል። ይህም ቤማንዳ ሰዎችን ማሰልጠን ብቻ ሳይሆን መማርን (ትምህርትን) በቀጥታ ከአጋጣሚ (ከወቅቱ) ጋር በማገናኘት ህይወትን እየለወጠ ስለመሆኑ ምስክር ነው ማለት ይቻላል።

ቤማንዳ ስልጠናን የተልዕኮ ማዕከሉ አድርጎ በመሥራት ላይ ነው። ተቋሙ በማይክሮሶፍት 365 ፣ SharePoint ፣ Power Platform ፣ Data migration ፣ AWS cloud computing እና በቅርቡ በMicrosoft Azure ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ፕሮግራሞችን እየሰጠ ይገኛል።

እነዚህ ፕሮግራሞች ንድፈ ሃሳባዊ ብቻ ሳይሆኑ በተግባር የተደገፉ ናቸው፡፡ ይህም ተሳታፊዎች በዓለም ዙሪያ ኢንዱስትሪዎችን በሚቀይሩ መሣሪያዎች ላይ ልምድ እንዲቀስሙ ያስችላቸዋል። በእነዚህ የስልጠና ውጥኖች ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ውስብስብ ዲጂታል ፈተናዎችን ለመወጣት እና በሥራ ቦታቸው ላይ አዳዲስ መፍትሄዎችን ለማምጣት ዝግጁ እንዲሆኑ ከፍተኛ እገዛ ያደርግላቸዋል።

የማማከር አገልግሎት (Consultancy): ቤማንዳ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል የማማከር አገልግሎት ሁለተኛው ነው፡፡ በእዚህም በሚሰጣቸው ጠንካራ የማማከር አገልግሎት አገልግሎቶች መልካም ስምን ገንብቷል።

ተቋሙ በርካታ ባለሙያዎችን ያቀፈ ቡድን በመያዝ ለተለያዩ ድርጅቶች - ባንኮችን፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን እና ሌሎች ተቋማት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። የማማከር አገልግሎቱ እንደየአስፈላጊነቱ የድርጅቶችን አሠራር በመፈተሸና ጥናት በማድረግ እንደገና እንዲዋቀሩ፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሠጡ ማሻሻል እንዲሁም ሠራተኞቻቸው በተቻላቸው መጠን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ዘመኑ የሚዋጀውን አገልግሎት በተቀላጠፈ አሠራር እንዲያከናውኑ እስከመርዳት ይደርሳል።

ሰራተኞች ሙያዊ ግቦችን ለማሳካት እንዲነቃቁ፣ እንዲደገፉ እና ክህሎትን የተላበሱ እንዲሆኑ ከማቻሉም በላይ ለእያንዳንዱ ድርጅት ፍላጎት የተበጁ የማማከር፣ የሙያ መመሪያ እና የምክር አገልግሎት ይሰጣል። ድርጅቶችን በሰው ሃብት እቅድ፣ በአመራር ልማት እና በሠራተኛ ማቆያ ስልቶች ሙያዊ ድጋፍ ይሠጣል፡፡ ይህ የማማከር ሥራ ሠራተኞች ሙያቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ ተቋማዊ አቅምን ያጠናክራል፤ እውቀትን ከተግባር ጋር ያገናኛል።

ሮቦቲክስ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI)፡ ሌላኛው የቤማንዳ ዓላማ ታዳጊዎችን መሰረት ያደረገ የሮቦቲክስ እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Arteficial intelligence- AI) ሥልጠና ማስፋፋት ነው። ይህ አዲስ ዘርፍ የቤማንዳ ራዕይ አካል ሲሆን፣ ወጣቶቻችንን በቅድሚያ ቴክኖሎጂን እንዲተዋወቁ ያደርጋል።

በተግባራዊ ወርክሾፖችና ፕሮግራሞች ልጆች ሮቦቶችን በመገንባት፣ AI እንዴት እንደሚሰራ በማስተማር፣ የወደፊት ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ያዘጋጃል። በዚህም ሀገራችን በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለምታደርገው ጉዞ አስተዋፅኦ ለማድረግ ተዘጋጅቷል።

የትምህርት ጥራትን ማሳደግ፡ በዚህ ረገድ የትምህርት ጥራትን በአራተኛ ደረጃ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ መንግሥት ለያዘው ፖሊሲ አጋዥ የሚሆኑ የLearning Management System (LMS) ትግበራን በማስተዋወቅና በማስፋፋት፣ የሀገሪቱን የትምህርትና ሥልጠና ጥራት በተቻለ መጠን እንዲሻሻል ያግዛል።

ማኅበራዊ ድጋፍ፡ የቤማንዳ ሚና ከንግድና ከቴክኖሎጂ በተጨማሪ፣ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ልማትና ማኅበራዊ ደህንነትን የሚያበረታቱ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ከአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አገልግሎት ይሰጣል።

የማህበራዊ ድጋፋን ለማጠናከርም የማህበረሰቡን ፍላጎቶች የሚያሟሉ ፕሮግራሞችን ማመቻቸት፣እንደ ትምህርታዊ አገልግሎት፣ ለወጣቶች መካሪነት እና ዲጂታል ማንበብና መፃፍ ማስቻል። ድጋፍ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን መደገፍ፣ የስልጠና አቅርቦት እና በሌላ መንገድ ሊገኙ የማይችሉ ግብአቶችን መስጠት ከውጥኖቹ መካከል ይገኙበታል።

ተቋሙ ማህበረሰቦችን በሚያጠናክሩ፣ ዲጂታል ማንበብና መጻፍን በሚያስተዋውቁ የቴክናሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የማህበረሰብ ክፍሎች በንቃት እንዲሳተፋ ያደርጋል።

ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር፣ ለወጣቶች ቴክኖሎጂን የማዳረስ ፕሮግራሞች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኖረዋል። ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ልማት እና ማህበራዊ ደህንነትን የሚያበረታቱ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ከአገር ውስጥ ዪኒቨርሲቲዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አገልግሎት ይሰጣል።

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.