Logo
Getu Temesgen
''የመጣሁት 20 ዓመቱን ለማካካስ ነው'' ጆኒ ራጋ

📌የኢትዮጵያ የመጀመሪያው አገር በቀል የሬጌ አርቲስት የሆነው ተወዳጁ ጆኒ ራጋ “ውሃ እና እሳት” በተሰኘ አልበም ተመልሶ መጥቷል!
#ethiopia | ከኢትዮጵያም አልፎም በመላው አፍሪካና ከዛም ባሻገር ከፍተኛ ተወዳጅነትን ባገኘው የመጀመሪያ አልበሙ ከምርጥ የሙዚቃ ቪድዮ አንስቶ እስከ የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ አርቲስት የተለያዩ እውቅናዎችን በማግኘት መንገዱን ያቀናው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አገር በቀል የሬጌ አልበም ላለፍት 20 ዓመታት ሁሌም እንዳዲስ ሲደመጥ ቆይቷል።

በነጠላ ዜማዎች፣ በመድረክ ሥራዎች ብሔም በሮያሊቲ መብት ተሟጋችነት ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ያልተለየው ጆኒ ራጋ በበርካታ አድናቂዎቹ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ሁለተኛ አልበሙን “ውሃ እና እሳት"ን መስከረም 21 ቀን 2018 ዓ.ም በጆኒ ራጋ ዩቲዩብ ቻናል እንካችሁ ይላል።

16 ሙዚቃዎችን በአንድ ላይ ይዞ እንደ ውሃ በተረጋጋ እድሜ ካሉት እራሱ ሙዚቀኛው “የኔ ዘመን ሰዎች" ከሚላቸው ትውልዶች እንደ እሳት ግለት እስካለበት አዲሱ ትውልድ ድረስ በሁለቱ ኃይላት በተወከሉ ሁለት አልበሞች በኩል ጆኒ ራጋ ለሁሉም መልዕክት አዘጋጅቷል።

ከአንጋፋ እስከ ወጣት ድምጻውያን ከጆኒ ጋር በጥምረት ብቅ ባሉበት በዚህ አልበም ጋሽ ባህታ ገብረሕይወት፣ ዮሐና፣ ናቲማን፣ ልጅ ሚካኤል፣ ኤደን አይሸሸም ፣ ዮሴፍ ኤቢሶ "እና ኤቨርሬጽ የተሳተፋ ሲሆን እንደውሃ ለተገለጸው ሩትስ 'እና ላቨርስ አይነት፣ በእሳት ለተወከለው ደሞ እንደ ራጋ እና ዳንስሆል ያሉ የሬጌ ንዑስ ዘርፎች ተካትተውበታል።

“የቆየሁባቸው ሃያ ዓመታት ነበልባል የሆነ እልህ ፈጥሮብኛል ውስጤ" ሲል በቅርቡ በራሱ ዩቲውብ ቻናል ላይ ከአድናቂዎቹ በማሕበራዊ ሚድያ ለተሰበሰቡ ጥያቄዎች መልስ በሰጠበት ልዩ ቃለመጠይቅ የገለጸው ጆኒ ራጋ “አሁን ስቱድዮ የተመለስኩትሃያ ዓመቱን ለማካካስ ነው:: ከዚህ በኋላ በጣም ብዙ ሰራዎች በተከታታይ ከኔ ይወጣሉ።'' ሲል አክሏል።

የውሃ እና እሳት አልበም ግጥም፣ ዜማ እና ቅንብር በራሱ በጆኒ ራጋ የተሰናዳ ሲሆን ፍቅር፣ ትዝታ፣ ፍርድ የጾታ እኩልነት እና ሕይወት በውሃ እና እሳት አልበም ከተነሱ ርዕሶች መሃል የሚጠቀሱ ናቸው። ስቱድዮ ውስጥ የተቀጹ መሳሪያዎችን ባካተተው በዚህ አልበም አንጋፋው ሙዚቀኛ ቶሚ ቲ (ቶማስ ጎበና) አሻራውን ያሳረፈበት ሲሆን እንደቀድሞ ሥራው ሁሉ በመላው ዓለም በጥራት መደመጥ እንዲችል ሚክሲንግ እና ማስተሪንጉ የተለያዩ አገሮች በሚገኙ የተመረጡ ስቱድዮዎች ተከውኗል።

የውሃ አልበም ሚክሲንግ በኒኮላስ ሴላምቢን 12H ስቱድዮ ፈረንሳይ ውስጥ እንዲሁም በታንድራ ጀግሯት ጃማይካ በሚገኘው ሚክሲንግ ላብ የተሰራ ሲሆን ማስተሪንጉ ደግሞ በሰባስቲያን “ሜሔው ሙድ" ሆውት ፈረንሳይ ባለውበዋይዝ ስቱድዮ ተጠናቋል።

እሳት የተሰኘው አልበም:- ሚክሲንግ በታንድራ ጀግሯት -በሚክሲንግ ላብ (ጃማይካ)፣ አዮሚፓሲ ቪክተር አዩዋሌ በዋርድረም ሚክሲንግ ስቱድዮ (ዩናይትድ ኪንግደም)፣ በኪሩቤል ተስፋዬ - ቶራ ስቱድዮ (ኢትዮጵያ) እና በቤን ጸብሰብስቴሸን (ፈረንሳይ) ተሠርቶ ማስተሪንጉ ደግሞ በሶነስ (ዩናይትድ ኪንግደም) ፣ በቤን ደብሰብስቴሸን (ፈረንሳይ) እና በኪሩቤል ተስፋዬ - ቶራ ስቱድዮ (ኢትዮጵያ) ተከሽኗል።

የተለያዩ የአርቲስቱ አድናቂዎች፣ ወዳጆች፣ የሙዚቃና የሚድያ ባለሞያዎች እንዲሁም ልዩ ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በማሪየት ኤግዚክዩቲቭ አፓርትመንትስ በተካሄደ የአልበም ቅምሻ ሰነ-ስርዓት የአርቲስት ጆኒ ራጋ የመጀመሪያ አልበም “ቁልፋን ሰጪኝ” 20ኛ ዓመት እና የሁለተኛ አልበሙ “ውሃ እና እሳት” ደግሞ አዲስ ጅምር ሆኖ ተከብሯል።

9 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.