Logo
YenetaTube
ታዋቂው የፍርድ ቤት ዳኛ ፍራንክ ካፕሪዮ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ዳኛ ካፕሪዮ በእጃቸው የፍርድ መዶሻ፣ በደረታቸው የሩህሩህ ልብ ባለቤት መሆናቸው ይነገርላቸዋል።

ዳኛው በጥልቅ ርህራሄያቸው፣ በትህትናቸውና በሰዎች መልካምነት ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት በዓለም ዙሪያ ተወዳጅ ነበሩ።

በፍርድ ቤት ስራቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ የነኩ ሲሆን፣ በሰብዓዊነት ምሳሌነታቸው ደግሞ ብዙ ሰዎች ያውቋቸዋል።

እሳቸውን ለማወቅ ወይም ቃላቸውን ለመስማት ዕድሉን ያገኙ ሁሉ፣ ስለቀልዳቸውና ደግነታቸውን ይመሰክራሉ።

እሳቸው የተከበሩ ዳኛ ብቻ ሳይሆኑ አባት፣ አያት፣ ቅድመ አያት እና ወዳጅ እንደነበሩም ይገለጻል።

ዳኛው በርህራሄ፣ በመግባባትና በልባዊ ፍቅራቸው ይታወሳሉ። በህልፈታቸውም የዓለም መገናኛ ብዙሃን በአንድ ቃል የሀዘን ዜና ይዘው ወጥተዋል።

ይህ ዜና የዓለም ሩህሩሁ ዳኛ ፍራንክ ካርፒዮ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋውን የሚያትት ነው። ዜናው የዓለም ልበቅኑ ዳኛ በ88 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉን ያትታል።

የፕሮቪደንስ ሮድ አይላንድ መዘጋጃ ቤት ዳኛ የነበሩት ፍራንክ ካፕሪዮ መዶሻቸው የህግ አንቀፆችን ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነትን ለማወጅ የሚታዘዝ ነበር። ይህም በመላው ዓለም ብዙ ወዳጅና አድናቆት እንዲቸራቸው አድርጓቸዋል።

በራሳቸው የቴሌቪዥን ዝግጅትም በዓለማቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያተረፉት ዳኛው፣ በፍርድ ወንበር ላይ ለተቀመጡ ሁሉ በሚያሳዩት ርህራሄ እውቅ ናቸው።

በዳኝነት ሚዛን ህጉ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነትም እንደሚፈርድ ያስመሰከሩት ዳኛው፤ ተከሳሾችን የሚያናግሩበት የትህትናና የመረዳት እንዲሁም የወዳጅ ያህል ቀለል ማለት ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የዓለም አገራት በርካታ አድናቂዎችን አስገኝቶላቸዋል።

ይሄ ርህራሄ በቀላሉ የመጣ ሳይሆን በመኖር ያገኙት መሆኑ ይገለጻል።

አነስተኛ የገቢ ምንጭ ካላቸው ቤተሰቦቻቸው የተገኙት ዳኛው ህይወትን ለማሸነፍ በብዙ መውጣት መውረድ ውስጥ አልፈዋል።

በታዳጊነት ዘመናቸው ህይወትን ለማሸነፍ ጫማ በማፅዳት፣ ጋዜጣ በማከፋፈልና ወተት የጫነ መኪና ላይ ሰርተዋል።

በልጅነት ዘመናቸው ታግለው ያሸነፏት ዓለም በማምሻ ዘመናቸውም ከጣፊያ ካንሰር ጋር አታግላቸዋለች።

ዳኛው ከጣፊያ ካንሰር ጋር መታገላቸውን ይፋ ካደረጉበት 2023 ጀምሮ ህይወታቸው ሊያልፍ የሰዓታት ዕድሜ እስከቀረበት ድረስ አድናቂዎቻቸውን በፀሎት እንዲያስቧቸው ተማፅነው ነበር።

ሞታቸውን ይፋ ያደረጉ ቤተሰቦቻቸውም እርሳቸው የተከበሩ ዳኛ ብቻ ሳይሆኑ ተወዳጅ ባል፣ አባት አያትና ቅድመ አያት እንደነበሩ መስክረዋል።

በፈረንጆቹ የጊዜ ቀመር በ1985 የተጀመረው የዳኝነት ጉዟቸው በጡረታ እስከተሰናቱበት 2023 ድረስ የዘለቀ ነበር ሲል ኒውዮርክ ፖስት ዘግቧል።

ዳኛው ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት የሰባት የልጅ ልጆች አያትና የሁለት የልጅ ልጅ ልጆች ቅድመአያት ነበሩ።

Gazette Plus ጋዜጣ ፕላስ

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.