Logo
Getu Temesgen
በመዲናዋ ሰሌዳ ሳይፈታና መንጃ ፈቃድ ሳይወሰድ ቅጣት የሚፈጸምበት አሠራር መጀመሩ ተገለጸ
#ethiopia | በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አሽከርካሪ የደንብ ጥሰት በሚፈጸምበት ወቅት፤ ሰሌዳ ሳይፈታበትና መንጃ ፈቃድ ሳይወሰድበት ቅጣት የሚፈፅምበትን አሰራር መጀመሩን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።

የባለስልጣን መስሪያቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ታረቀኝ በተለዩ አንዳንድ ምክንያቶች ሰሌዳ ሊፈታ እንደሚችል አንስተው፤ ከእነዚህም ውስጥ አሽከርካሪው ቅጣት ተቀጥቶ ደረሰኝ እጁ ላይ ካለ እና ከተቀጣ በኋላ መንጃፈቃድ ሲጠየቅ ማሳየት የማይችል ከሆነ ያለው አማራጭ ሰሌዳ መፍታት እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህ ሲሆንም ከተቀጣበት ቦታ ቤቱ ድረስ እስኪሄድ አልያም የመንግሥት ተቋማት ላይ ሂዶ ሕጋዊ ሂደቱን ተከትሎ ክፍያ ከፈፀመ በኋላ፤ መውሰድ እንዲችል እንጂ አገልግሎት እንዲሰጥበት አለመሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የተከለከለ ቦታ ላይ ከቆመ እና አሽከርካሪው ከሌለ ሰሌዳው ሊፈታ እንደሚችል አንስተዋል።

በመሆኑም ተቆጣጣሪዎች በእነዚህ አይነት ምክንያቶች አሁንም ቢሆን ሰሌዳ የሚፈቱበት አጋጣሚ እንዳለ ገልጸዋል።

ነገር ግን ሰሌዳን መፍታት ለወንጀል ነክ ጉዳዮች የሚያጋልጥበት ዕድል እና ሰሌዳዎች በውጪ ምንዛሬ የሚመጡ በመሆናቸው እየተፈቱ በሚታሰሩበት ወቅት የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ስለመኖሩ አንስተዋል።

በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሲባል ሰሌዳ ሳይፈታ እና መንጃ ፈቃድ ሳይቀበሉ የሚተገበርበትን መንገድ ለመፍጠር በቴክኖሎጂ የታገዘ ስርዓት መጀመሩን አስታውቀዋል።

በዚህ ስርዓትም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የብቃት ማረጋገጫ ያላቸው አሽከርካሪዎች እና ከ 800 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች መረጃ መወሰዱን ለአሐዱ ተናግረዋል።

መረጃውን በመያዝ ቅጣት ለመፈጸም በሚደረግበት ሂደት ግን በተለይም ቆየት ያሉ ተሽከርካሪዎች የተመዘገቡበት ስልክ ቁጥር በቤት ስልክ በመሆኑ፤ አሽከርካሪዎች ቅጣት የከፈሉበት የማረጋገጫ መልዕክት በስልካቸው መግባት አለመቻሉ ተግዳሮት ስለመሆኑ አንስተዋል።

በመሆኑም አሰራሩ መጀመሩን ገልጸው፤ ይህንን ችግር አስወግዶ በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር ዝግጅት መጨረሱን ተናግረዋል።

"ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶችና ሌሎች የተለየ ችግር ካልገጠመ በስተቀር በአዲስ አበባ ውስጥ ሲስተም ላይ የተመዘገቡ መንጃፈቃድ እና የተሽከርካሪ ሰሌዳዎችን ሳይፈቱ እና መንጃፈቃድ ሳንቀበል ተግባራዊ እያደረግን ነው" ብለዋል። #ahaduradio

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.