Logo
FastMereja
“የምድር ጌጥ ኢትዮጵያ” ታሪካዊ አውደ ርዕይ የመጎብኛ ጊዜ መራዘሙ ተገለጸ
#fastmereja I የሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ሥራ ድርጅት ያዘጋጀው እና የልጆች እንዲሁም የቤተሰብ ታሪካዊ አውደ ርዕይ የሆነው "የምድር ጌጥ ኢትዮጵያ" የመጎብኛ ጊዜ ለተጨማሪ ሳምንታት መራዘሙን ተቋሙ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ።

ዛሬ መስከረም 13 ቀን 2019 ዓ.ም በተሰጠው በዚህ መግለጫ፤ አውደ ርዕዩ ከመስከረም 30 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ሳምንታት በየሳምንቱ ቅዳሜ እና እሁድ ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንዲጎበኝ መወሰኑ ተገልጿል።

ይህ አውደ ርዕይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከጥንት እስከ አሁን የኖረችበትን ወርቃማ የታሪክ ጉዞ የሚተርክ ሲሆን፤ ህጻናት እና ቤተሰቦች ታሪካቸውን፣ ሃይማኖታቸውን እና ሀገራዊ ማንነታቸውን በተለያየ የስሜት ህዋሳት (በማየት፣ በመዳሰስ፣ በመስማት እና በመቀምስ) እንዲረዱ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

አውደ ርዕዩ በሆላንድ ኤምባሲ ጀርባ በሚገኘው ሆላንድ ፓርክ ውስጥ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ሰፊ የዝግጅት ስራዎች ተከናውነውበታል።

እንደ አዘጋጆቹ መግለጫ፤ አውደ ርዕዩ ቀደም ሲል ለተወሰኑ ቀናት ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም፣ በህዝቡ በኩል በቀረበው ከፍተኛ ጥያቄ እና የታሪክ እሴቱን ለበርካቶች ለማዳረስ ካለው እቅድ አንጻር የመጎብኛ ጊዜው እንዲራዘም ተደርጓል።

በመሆኑም መስከረም 30 እና ጥቅምት 1፣ ጥቅምት 7 እና 8 እንዲሁም ጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2019 ዓ.ም ህብረተሰቡ በሆላንድ ፓርክ ተገኝቶ እንዲጎበኝ የሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ሥራ ድርጅት ጥሪውን አስተላልፏል።

13 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.