Logo
Getu Temesgen
18ኛው የብሪክስ ጉባኤ በሕንድ፡
የአባል ሀገራት መሪዎች ወደ ኒው ዴልሂ እየገቡ ናቸው
#ethiopia | በሕንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የአባል ሀገራት መሪዎችና ከፍተኛ ልዑካን ወደ ኒው ዴልሂ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ይህ ታሪካዊ ጉባኤ በነገው ዕለት በይፋ የሚጀመር ሲሆን፣ ከዋናው መርሃ ግብር አስቀድሞ በርካታ የሁለትዮሽ እና የብዙ ወገን የምክክር መድረኮች በስፋት እየተካሄዱ ይገኛሉ።

ከመሪዎች ጉባኤው መከፈት ቀደም ብሎ በሕንድ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የብሪክስ የንግድ መድረክ ተካሂዷል።

መድረኩ በአባል ሀገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ማጠናከር በሚያስችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የዘርፉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የንግድ ማህበረሰብ መሪዎች ተሳትፈውበታል።

ከጉባኤው ውጭ ባሉ የጎንዮሽ መድረኮች የመሪዎች ከፍተኛ የምክክር ስብሰባዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኒው ዴልሂ ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት፣ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ግንኙነት እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ምክክር አድርገዋል።

በተመሳሳይ የምሽት ስብሰባ የኢራኑ ፕሬዚዳንት መሱድ ፐዜሽኪያን፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በጋራ ተገናኝተው በስብስብ ሀገራቱ የወደፊት አቅጣጫዎችና የጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በቀጣዮቹ ሰዓታት የሌሎች አባል ሀገራት መሪዎችና ልዑካን ኒው ዴልሂ ይደርሳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ነገ በሚጀመረው ጉባኤ ላይ በሀገር ውስጥ ገንዘቦች የመገበያየት ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ማሻሻያ፣ የታዳጊ ሀገራትን ድምፅ በዓለም መድረክ ማሳደግ እንዲሁም የብሪክስ አባልነትና የአጋርነት ማዕቀፎችን መገምገም በዋናነት ትኩረት የሚያገኙ ጉዳዮች ናቸው።

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#brics #bricssummit #india #newdelhi #diplomacy #economy #putin #modi #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa

25 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.