Logo
EBC
ዘመንን በሥራ መዋጀት፦ ኢትዮጵያ በአዲስ ዓመት የሰነቀችው ተስፋ
***************

ፈጣሪ ለሰው ልጅ ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ እጅግ ውዱ እና ለሁሉም እኩል የተቸረው ጸጋ ጊዜ ነው።

ዘመን ለአዲስ ዕድል እና ለላቀ ከፍታ ትልቅ በር ቢሆንም፤ በሀገር እና በትውልድ ሕይወት ውስጥ የሚፈጠር እውነተኛ ልዩነት ግን በጊዜው ማለፍ ብቻ ሳይሆን፣ በዚያ ዘመን ውስጥ በሚከናወን የሥራ ውጤት እና የላብ ፍሬ የሚወሰን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ "ዘመን ዕድል ነው፤ ዘመንን መጠቀም ግን የሥራ ውጤት ነው፤ ዘመንን ፈጣሪ ለሁላችንም በእኩልነት ሰጥቶናል፤ ልዩነት የሚፈጠረው ግን በዘመን በመሥራት እና ባለመሥራት ነው" ሲሉ የገለጹት ጥልቅ ሀሳብ ይህን እውነት የሚያረጋገጥ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ይህን ሕያው እውነት መሬት አስረግጣ በተግባር እያሳየች ትገኛለች። የተሰጣትን ዘመን በከንቱ ሳታሳልፍ፣ የዜጎቿን ዕውቀት እና ጉልበት አስተባብራ ወደ ታላቅ የልማት እና የማንሠራራት ምዕራፍ ተሸጋግራለች።

ሀገራችን ዘመንን በፍሬ የማስጌጥ ጥበቧን በየስፍራው በሚታዩ የልማት ሥራዎቿ እያረጋገጠች ነው።

በትናንት ስብራቶች ሳንበገር በየማሳዎቻችን ላይ በስንዴ እና በቡና ምርት የፈጠርነው አብዮት፣ በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ አዲስ ሕይወት በዘሩት አምራች ፋብሪካዎቻችን እንዲሁም በ"መሶብ" እና መሰል ዘመናዊ ዲጂታል አውታሮች የተዘረጋው ቀልጣፋ አሠራር የዚሁ ሥራ ባህል ፍሬዎች ናቸው።

ይህ በልፋት ያገኘነው የልማት ስኬት እና እየተገነባ ያለው ግዙፍ የማምረት አቅም ግን ያለ ገደብ ወደ ዓለም ገበያ መውጣት ይኖርበታል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከአዲስ ዓመት ተስፋችን ጋር በቀጥታ የሚገናኘውም እዚህ ላይ ነው።

በግብርናውም ሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመረተው ምርት የላቀ ትርፍ የሚያስገኘው፣ የራሳችን የሆነ አስተማማኝ የባሕር በር እና የሎጅስቲክስ መውጫ ሲኖረን ነው።

ስለዚህም ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ከምትሰንቃቸው ታላላቅ ተስፋዎች መካከል የኢኮኖሚ ዕድገቷን የሚያፋጥነውን እና ብልጽግናዋን የሚያረጋግጠውን የባሕር በር ባለቤትነት ዕውን ማድረግ አንዱና ዋነኛው ነው።

ዘመንን የመጠቀም ትልቁ ምስጢር በዛሬው አዲስ ትውልድ ላይ ይንጸባረቃል። አካባቢያዊ ማንነቱን ከሀገራዊ ታላቅነቱ ጋር አዋህዶ ያስማማ፣ ጋራ እና ሸንተረሩን በደንና በምርት ለመሸፈን ሌት ተቀን በቁርጠኝነት የሚተጋ አዲስ አርበኛ ትውልድ ተፈጥሯል።

በየዘርፉ የተቀመጡ ሀገራዊ ዕቅዶቻችንን በጥራት እና በጊዜ በማጠናቀቅ፣ ዘመናት የወለዷቸውን ስብራቶች በምክክርና በሽግግር ፍትሕ በማከም እንዲሁም ውስብስብ ግጭቶችን በውይይት በመፍታት ረገድ ያስመዘገብናቸው ስኬቶች የዚሁ ዘመኑን የተገነዘበ ትውልድ ውጤቶች ናቸው።

አሁን አዲስ ዘመንን ልንቀበል ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውናል። ይህ የሚተካው ዘመን አዲስ ዕድል እና አዲስ ተስፋን ይዞ የሚመጣ ሲሆን፣ ያን ዕድል ተጠቅመን በኢኮኖሚ ራሷን የቻለች እና የባሕር በር ራዕይዋን ያሳካች የበለፀገች ኢትዮጵያን የመገንባት ኃላፊነት በሁላችንም ትከሻ ላይ ወድቋል።

በአዲሱ ዓመት የገጠሙንን ፈተናዎች ተሻግረን፣ ዘመኑን በሥራ በመቀየር የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ በጋራ እናፋጥናለን።

በሔዋን ጌታቸው
#ethiopia #ethiopiannewyear #ethiopiarising #ethiopiatamrit #economicgrowth #ebc

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.