Logo
EBC
ኃያላኑን ከኢትዮጵያ ጎን ያሰለፉት የለውጥ ፍሬዎች
*************

ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም የጀመረችው የለውጥ ጉዞ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መዋቅሮቻችንን በስር ነቀል ሁኔታ ያሻገረ ታሪካዊ ክስተት ነው።

በለውጡ መባቻ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶች መጋጨት ፈጥሮት የነበረው ውዥንብር፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች በጥርጣሬ ፊታቸውን እንዲያዞሩብን አድርጎ ነበር።

ይሁን እንጂ የተጋረጡትን ውስብስብ ፈተናዎች በጽናት በማለፍ እና ማዕከላዊ መስመሯን በመጠበቅ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችው ሁለንተናዊ ዕድገት እነዚህን አጋሮች ወደ ትብብር መድረክ በድጋሚ መመለስ ችሏል።

በተለይም ከአሜሪካ እና ከሌሎች ምዕራባውያን አጋሮች ጋር የታደሰው ስትራቴጂያዊ ትብብር የዚሁ የጸና የዲፕሎማሲ እና የለውጥ ጉዞ አንዱ ማሳያ ነው።

ይህ የአጋርነት መታደስ በተጨባጭ በተተገበሩ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች የተገኘ ውጤት ነው።

ሐምሌ 2016 ዓ.ም የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉን ተከትሎ፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የነበራቸውን ስጋት አንስተው ወደ ሙሉ አጋርነት ተመልሰዋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያጸደቀው የ3.4 ቢሊዮን ዶላር እና የዓለም ባንክ የ10.7 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ የዚሁ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ፍሬዎች ናቸው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተፈላጊነት፣ ሰፊ የገበያ ተደራሽነት እና ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት በግልጽ ያረጋገጠ ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው።

ከዚህ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድል ባሻገር፣ ኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመኗን የሚያደምቁ እና ብሩህ ተስፋን ሰንቀው የተጠናቀቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በተግባር አሳይታለች።

ከእነዚህም ግንባር ቀደሙ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተደረገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ነው። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አማካኝነት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የስንዴ ምርትን ከውጭ መግዛት ከማቆም አልፈን ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምረናል።

ለዚህም ታሪካዊ ስኬት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ጥር 2016 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁን የአግሪኮላ ሜዳሊያ አበርክቷል።

በሌላ በኩል በአፍሪካ ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁ እና በከፍተኛ አቅም ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የብልጽግናችን አንዱ እና ዋነኛው ምሰሶ ሆኖ ቀጥሏል።

በከተማ ልማት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎችም አስደናቂ ለውጦች ተመዝግበዋል።

በአዲስ አበባ እና በሌሎች ክልል ከተሞች የተተገበረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የእግር መንገዶችን፣ የአረንጓዴ ስፍራዎችን እና የዘመናዊ ከተማ መሠረተ ልማቶችን በጥበብ በማቀናጀት የከተማ መሬት አጠቃቀምን ሙሉ ለሙሉ አዘምኗል።

በተመሳሳይ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋናችንን ወደ 23.6 በመቶ ማሳደግ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ አበርክቶው ከፍተኛ ዕውቅና አስገኝቷል።

በዲጂታል ዘርፍ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂ ጠንካራ መሠረት በመጣል ለ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ዕቅድ መድረኩን አመቻችቷል።

የበርካታ ሚሊዮን ዜጎችን የዕለት ተለት እንቅስቃሴ እያዘመነ የሚገኘው የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ፣ እንዲሁም የቴሌብር፣ የ5ጂ አገልግሎት እና የኢ-ኮመርስ ቴክኖሎጂዎች መስፋፋት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታችንን በከፍተኛ ደረጃ እያፋጠኑት ይገኛሉ።

ከተወሳሰቡ ፖለቲካዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ፈተናዎች ወጥተን በማዕከላዊው የመደመር መስመር ላይ በመቆም ታሪካችንን በድል አድራጊነት እየጻፍን እንገኛለን።

እውን የሆኑት እጅግ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እና ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር ዳግም የተገነባው ስትራቴጂያዊ አጋርነት ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የማትበገር እና በዘላቂ ብልጽግና ጎዳና ላይ የምትገኝ መሆኗን በተጨባጭ ያረጋግጣሉ።

በቀጣይም ይህ የጸና የለውጥ ጉዞ ለዜጎቻችን የላቀ የኑሮ ደረጃን የሚያረጋግጥ፣ እንዲሁም ለቀጣናው የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ትስስር ማዕከልነታችንን ይበልጥ የሚያጠናክር ይሆናል።

በለሚ ታደሰ
#ethiopia #economicreform #digitalethiopia #greenlegacy #gerd #brics #ebc

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.