Logo
EBC
የባሕር በር ባለቤትነት፤ የትውልዱ ታሪካዊ ኃላፊነት
***************

ኢትዮጵያ በንግድና በሸቀጥ ልውውጥ የብዙ ሺህ ዓመታት የንግድ ታሪክ ባለቤት ናት። ከጥንት ጀምሮ ንግድ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ የዘለቀ ሲሆን፤ ከጎረቤት አገራት፣ ከቀጣናው አልፎም ከሩቅ ዓለም ጋር የነበራት የንግድ ትስስር እጅግ የጠነከረ ነበር።

የታሪክ ድርሳናት እንደሚመሰክሩትም፣ ኢትዮጵያ ለዚህ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ዋነኛው መተንፈሻና መገናኛ ደግሞ በቀይ ባህር በመጠቀም የምታደርገው የንግድ እንቅስቃሴ ነበር።

ዛሬ ላይ የንግድ መንገዶቹ ዘምነው በየብስ፣ በባቡር፣ በአየርና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ቢተኩም፤ መሠረታዊው ፍላጎት ግን አሁንም አልተቀየረም። ይህም ምርትን ለሰፊው የዓለም ገበያ ማቅረብና ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ከዓለም አቀፉ የንግድ ሥርዓት ጋር ማስተሳሰር ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው አገራት አንዷ መሆኗ፣ የንግድና የሎጂስቲክስ ፍላጎቷን እጥፍ ድርብ አድርጎታል።

ምርቶችን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ፣ ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ግብዓቶችን ለማስገባትና በዓለም አቀፍ የንግድ ውድድር ውስጥ ውጤታማ ተዋናይ ለመሆን የባህር በር አማራጭ መኖር ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።

የዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያ ገና ከጥንት ጀምሮ የነበራትን የታሪክ እውነታ መሠረት በማድረግ፣ የባህር በር ጥያቄን በሰለጠነና በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ የመመለስ የታሪክ ኃላፊነት አለበት።

ይህ ጥያቄ የመልክዓ ምድር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ ከኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከሎጂስቲክስ ቅልጥፍና፣ ከሀገራዊ ደኅንነትና ከቀጣናዊ ትስስር ጋር የተያያዘ የዘመናችን ወሳኝ አጀንዳ ነው።

የአሞሌ ጨው በግመልና በበቅሎ ተጭኖ የሚጓዝበት ዘመን ቢያልፍም፣ ንግድ ሁልጊዜም መንገድ እንደሚፈልግና መንገድ ደግሞ ሰዎችንና አገራትን እንደሚያገናኝ የሚያሳየው መሠረታዊ እውነት ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

በመሆኑም ከጥንቱ የአሞሌ ጨው ንግድ የጀመረውን ጉዞ ዳር ለማድረስ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የጀመረችውን ዲፕሎማሲያዊ ትግል አጠናክራ ልትገፋበት ይገባል።

በልዩ እሸቱ
#ebc #ethiopiatrade #maritimeaccess #redsea #economicdiplomacy #ethiopiarising #regionalintegration

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.