Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው 'ማሪን ዋን' የተሰኘው ሄሊኮፕተር፣ በዋሽንግተን ዲሲ የአየር ክልል ውስጥ ከኤንቮይ ኤር የመንገደኞች አውሮፕላን ጋር ከመጋጨት ለጥቂት ማምለጡን ተከትሎ የአሜሪካ አቪዬሽን ባለስልጣናት ጥብቅ ምርመራ ጀመሩ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሎስ አንጀለስ የሚያደርጉትን በረራ ለመጀመር ማክሰኞ ዕለት ከዋይት ሀውስ ወደ ጆይንት ቤዝ አንድሪውስ በሄሊኮፕተራቸው እያመሩ ሳለ አደጋው ሊከሰት መቃረቡን ዘ ዋል ስትሪት ጆርናል ዛሬ በዘገባው አጋልጧል። የደህንነት ፕሮቶኮሎች እንደሚያስገድዱት፣ የፕሬዝዳንቱ ሄሊኮፕተር በአየር ላይ በሚሆንበት ወቅት በአቅራቢያው በሚገኘው የሮናልድ ሪገን ዋሽንግተን ብሔራዊ አውሮፕላን ማረፊያ የንግድ በረራዎች መቋረጥ የነበረባቸው ቢሆንም፣ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ይህንን የደህንነት አሰራር ባለማክበራቸው ሁለቱ አውሮፕላኖች እጅግ አደገኛ ወደሆነ ቅርበት ሊመጡ ችለዋል።

ለፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (FAA) የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደገለጹት፣ ሄሊኮፕተሩ እና የመንገደኞች አውሮፕላኑ በጎን 1.3 ኪሎ ሜትር (0.8 ማይል) እንዲሁም ከላይ እና ታች በ213 ሜትር (700 ጫማ) ርቀት ላይ ብቻ ተገናኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ሁለቱም በሰላም ማረፋቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎቹ አውሮፕላኖቹ ርቀታቸውን እስኪጠብቁ ድረስ የቅርብ ግንኙነት ማድረጋቸውን አስተዳደሩ አስታውቋል። የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይም በበኩላቸው "ፕሬዝዳንቱ በምንም ዓይነት አደጋ ውስጥ አልነበሩም" ሲሉ አረጋግጠዋል። አሁን ላይ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር እና የብሔራዊ ትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ በጉዳዩ ላይ የጋራ ምርመራ እያካሄዱ ይገኛሉ።

ይህ አሳሳቢ የደህንነት ጥሰት የተፈጠረው፣ በጥር 2025 የአሜሪካ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን እና የአሜሪካ ጦር 'ብላክ ሆክ' ሄሊኮፕተር ተጋጭተው 67 ሰዎች (በአውሮፕላኑ የነበሩ 64 መንገደኞች እና 3 የሄሊኮፕተር አብራሪዎች) ህይወታቸውን ካጡበት አሰቃቂ አደጋ በኋላ መሆኑ ትኩረት ስቧል።

በወቅቱ ወደ ፖቶማክ ወንዝ በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ህይወታቸውን ካጡት መካከል፣ ከካንሳስ የአሜሪካ ፊገር ስኬቲንግ ሻምፒዮና ሲመለሱ የነበሩ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች እና ቤተሰቦቻቸው ይገኙበታል። ከእነዚህም ውስጥ በ1998 ወደ አሜሪካ በማምራት በአሰልጣኝነት ሲሰሩ የነበሩት የ1994ቱ የዓለም ሻምፒዮን ሩሲያውያን ኦሎምፒያኖች ቫዲም ናኡሞቭ እና ዬቭጄኒያ ሺሽኮቫ ይገኙበታል። ያንን የጥር ወር አደጋ ተከትሎ፣ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በሮናልድ ሪገን አውሮፕላን ማረፊያ ዙሪያ የሄሊኮፕተር በረራዎችን በቋሚነት የገደበ ሲሆን፣ ማሪን ዋን በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የንግድ በረራዎች ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጡ ጥብቅ አሰራር ተግባራዊ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።

22 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.