Logo
FastMereja
በኮንታ ዞን ሙሉ በሙሉ ተፈጥሯዊነቱን የጠበቀ አዲስ የጫካ ቡና መገኘቱ ተበሰረ!
#fastmereja :-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚገኘው ታሪካዊው ኮንታ ዞን፣ እስከ ዛሬ በሰው እጅ ያልተነካና ተፈጥሮአዊ ይዘቱን ሙሉ በሙሉ ጠብቆ የቆየ አዲስ የጫካ ቡና (Wild Forest Coffee) ተበሰረ።

ይህ በሰው እጅ ያልተተከለና «ያልተመነዘረ አረንጓዴ ወርቅ» የተባለው አዲስ የቡና ዘር የተገኘው፣ በኮንታ ዞን «ኦሽካ ዴንቻ» ጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ በሚገኘው «አሜክ ኤጄቻ» በተሰኘ ልዩ ቦታ ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን አካባቢው ሰውና የዱር እንስሳት በተስማማ ሁኔታ የሚኖሩበት በመሆኑ፣ የቡናው ተፈጥሯዊ መዓዛና ጣዕም እጅግ ልዩ እንደሆነ ተገልጿል።

ድርጅቱ አዲሱ የቡና ዘር መገኘቱ ለሀገራችን አዲስ ዓለም አቀፍ ብራንድ ይዞ የሚመጣ መሆኑን ጠቁሞ፤ እንደ ጅማ፣ ይርጋጨፌ እና ሐረር ሁሉ «Konta Coffee» በሚል ስም ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ በመቅረብ፣ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ብሏል።

በተጨማሪም ያልተነካውን የኮንታ የተፈጥሮ ጫካ እና የቡና መገኛ ቦታዎችን ለዓለም በማስተዋወቅ የኢኮ-ቱሪዝም ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያነቃቃው ገልጿል።

የኮንታ ብሔረሰብ የሙዚቃ አቀንቃኝና የባህል አምባሳደር አርቲስት ወንድወሰን አበበ (ወንዴ ኮንታ) በበኩሉ፣ “«ኑ ቡና ጠጡ» የሚለው ጥሪ የቡና መጠጣት ሥነ-ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የሰላም፣ የፍቅር፣ የጽኑ ጉርብትና እና የኢትዮጵያዊነት መስተጋብር ማሳያ ነው” ሲል ተናግሯል።

አርቲስቱ አክሎም ይህንን ውድ ተፈጥሮአዊ ሀብት ጠብቆ ላቆየው ማኅበረሰብ እውቅና መስጠትና ባህሉን ከኪነ-ጥበብ ጋር አዋህዶ ማቅረብ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን አብራርቷል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ ለዕይታ ያልበቁና በምስል ያልተቀረፁ የባህል ትውፊቶችን ቅርፃቸውን እንደጠበቁ ለዓለም መድረክ ለማብቃት ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል።

ይህንን ታሪካዊ ግኝት አስመልክቶ «ቶካ ፊልም መንደር እና ኢኮ ቱሪዝም» (Konta Coffee) በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አዲሱን የጫካ ቡና ይፋ ለማድረግ "ኑ ቡና ጠጡ" የተሰኘ ታላቅ ሀገራዊ ጥሪና የመርሃ ግብር ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።

በዚሁ መሠረት ቶካ ፊልም መንደር ከ«ኪን-ኢትዮጵያ የባህል ቡድን» እና ከ«ቤራ ኢንተርቴይንመንትና ኤቨንትስ» ጋር የጋራ የሥራ ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን፣ በቅርቡም በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

12 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.