Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ከትላንትናው እለት ጀምሮ 48 ዓይናለም ንጉሤ የሚመሩት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ባለስልጣን ሰራተኞች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። ይህ እርምጃ መንግስት በተለያዩ ተቋማት ላይ እየወሰደ ያለው ተከታታይ የእስር ዘመቻ አካል ቢሆንም፣ የዘመቻው አካሄድ እና ኢላማ ግን በፖለቲከኞች ዘንድ ጠንካራ ትችት እያስተናገደ ይገኛል።

የአሁኑ የገቢዎች እና ጉምሩክ ሰራተኞች እስር፣ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከተወሰዱ ተመሳሳይ የህግ እርምጃዎች ጋር ተዳምሮ የሚታይ ነው። ከዚህ እስር ቀደም ብሎ ሙፈሪያት ካሚል በምትመራው በስራና ክህሎት ሚኒስቴር ዜጎችን በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት ወንጀል የተጠረጠሩ ሰራተኞች በሙስና መታሰራቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ከወራት በፊት ከነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ የሙስና ወንጀል ካሳሁን ጎፌ የሜሩት የንግድ ሚኒስቴር ሰራተኞች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ አርሶ አደሩን በከፍተኛ ሁኔታ ካማረረው የማዳበሪያ አቅርቦት መጓተት እና ሙስና ጋር በተያያዘም የባህር ትራንዚት ሰራተኞች ተይዘው እንደነበር አይዘነጋም።

እነዚህ ተከታታይ የፀረ-ሙስና እርምጃዎች በታችኛው እና መካከለኛው የሰራተኛ እርከን ላይ ያተኮሩ መሆናቸው የዘመቻውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል። ፖለቲከኛ ጀዋር መሐመድ ይህንን ሁኔታ አስመልክቶ ባቀረበው ጠንካራ ትችት፣ እነዚህ ሁሉ ከሙስና ጋር የተያያዙ እስሮች አንድ ትልቅ ነገር እንደሚጎድላቸው አመላክቷል።

እንደ ጀዋር ትንታኔ ይህ መጠነ-ሰፊ እና የተደራጀ ሙስና በየተቋማቱ ሲፈፀም፣ የየመስሪያ ቤቶቹ ዋና ሀላፊ የሆኑት እና በሙስናው ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሆኑት ሚኒስትሮች ምንም አይነት የህግ ተጠያቂነት አልተደረገባቸውም። የፍትህ ስርዓቱ ዋና ዋናዎቹን የሙስና ጠንሳሾች ከመንካት ይልቅ፣ ጫፍ ላይ ያሉትን ፈፃሚዎች ብቻ ማሰሩ "ሻርኮቹን ትቶ ትናንሽ አሳዎችን ማጥመድ" ነው ሲል የፀረ-ሙስና ዘመቻውን ይዘት አጣጥሎታል።

ይህ እይታ የሙስና ችግር ስር ሰደድ መሆኑን እና እውነተኛ መፍትሄ ለማምጣት ከታችኛው እርከን ባለፈ ስልጣን ላይ ያሉ የዋና ተቋም መሪዎችንም በህግ ፊት እኩል ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.