Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በፌንቴክ ኢንቨስትመንት የመኪና ማጭበርበር ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥሮ በእስር ላይ የቆየው ቲክቶከር መንሱር ጀማል፣ የተፈቀደለትን የዋስትና ገንዘብ ከፍሎ ማምሻውን ከእስር በመለቀቅ ቤቱ መግባቱ ተሰማ። ይህንን ተከትሎም ተጠርጣሪው ቀሪ የፍርድ ቤት የህግ ሂደቶችን እና ክሱን በውጭ ሆኖ የሚከታተል ይሆናል።

ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት የሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ለቲክቶከሩ የ800 ሺህ ብር የዋስትና መብት መፍቀዱ ይታወሳል። የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ተጠርጣሪው ደስታ ቢሰማውም፣ የተጠየቀውን ከፍተኛ የዋስትና ገንዘብ ወዲያውኑ አቅርቦ መክፈል ባለመቻሉ ድንጋጤ ውስጥ ወድቆ እንደነበር የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደቱን ያስተባበሩ ግለሰቦች ለ'ዘ-ሀበሻ' ገልጸዋል። ይህንን ክፍተት ለመሙላትም በፍጥነት ወደ መዋጮ ማሰባሰብ ስራ በመግባት ገንዘቡን አሟልተው ክፍያውን በመፈጸም ዛሬ ከእስር ሊያስፈቱት ችለዋል።

በዋስትና ገንዘብ ማሰባሰቡ ሂደት ማን ምን ያህል ገንዘብ እንዳዋጣ የሚያሳይ ስክሪን ሾትን የመሳሰሉ ማስረጃዎች ቢኖሩም፣ አስተዋጽኦ ያደረጉት ወገኖች ማንነታቸው በምስጢር እንዲያዝ መፈለጋቸው ታውቋል። ግለሰቦቹ ስማቸው እንዳይገለጽ እና እንዳይታወቅ የሚፈልጉበት ዋነኛ ምክንያት፣ በፌንቴክ ማጭበርበር ገንዘባቸውን ካጡ ተበዳዮች ሊሰነዘርብን ይችላል ከሚል የጥቃት ስጋት እና ፍራቻ አንጻር መሆኑ ተጠቁሟል።

4 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.