Logo
EBC
የሀገርን ዕጣ ፈንታ ከፖለቲካ ልሂቃን እጅ ፈልቅቆ ለዜጎች ያስረከበው ሀገራዊ ምክክክር
*********************

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አንዱ የኅብረተሰብ ክፍል እንደ ወርቃማ የታሪክ ዘመን የሚያየውን፣ ሌላው እንደ ጭቆና እና መገለል ዘመን ሲመለከተው መኖሩ የተለመደ ክስተት ሆኖ ቆይቷል።

ይህ የተራራቀ የታሪክ ግንዛቤ እና ያልተፈቱ መዋቅራዊ ቅራኔዎች ሀገራችንን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለሚሸጋገር የትርክት ግጭት ዳርገዋታል።

ዘውዳዊውን ሥርዓት ተክቶ የመጣው ወታደራዊ አገዛዝም ሆነ፣ እርሱን ተከትሎ የመጣው የኢሕአዴግ ሥርዓት የዜጎችን የዴሞክራሲ፣ የፍትህ እና የእኩልነት ጥያቄዎች በዘላቂነት መፍታት አልቻሉም።

በተለይም ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የተዘረጋው የልዩነት ፖለቲካ፣ በዜጎች መካከል መጠራጠርን በማንገሥ የጋራ ሀገራዊ ማንነታችንን በጽኑ ፈትኖታል።

የ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ የፈጠረው የፖለቲካ መነቃቃት ትልቅ ተስፋን ያሰነቀ ቢሆንም፣ ከዴሞክራሲያዊ ባህል ማነስ እና ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት ጋር ተዳምሮ አዳዲስ ሀገራዊ ስጋቶችን መፍጠሩ አልቀረም።

ይሁንና ከእነዚህ ሁሉ ውጣ ውረዶች ኢትዮጵያውያን አንድ ትልቅ ትምህርት ቀስመዋል። ይኸውም ታሪካዊ እና መዋቅራዊ ቀውሶችን በጦርነት፣ በኃይል እና በአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ለመፍታት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ጊዜያዊ ማስታገሻ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ ነው።

እውነተኛው መፍትሔ ያለው ጠብመንጃን አስቀምጦ በጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ፣ በመደማመጥ እና በሀሳብ ልዕልና በማመን ላይ ብቻ መሆኑ ታምኖበታል።

ይህን ታሪካዊ የዕይታ ሽግግር እውን ለማድረግ ነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው። ከተቋሙ አወቃቀር ጀምሮ ሂደቱ ፍፁም የተለየ ነበር።

ከመነሻው፣ ከ632 እጩዎች ውስጥ በሕዝብ ተሳትፎ የተመረጡ 11 ኮሚሽነሮች ገለልተኛ ሆነው ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ተደርጓል።

ይህ እርምጃ የፖለቲካ ልሂቃን ብቻ የሀገርን ዕጣ ፈንታ ሲዘውሩበት የነበረውን ባህል በመስበር፣ መሠረታዊው ዜጋ የሀገሩን ዕጣ ፈንታ በራሱ እንዲወስን ዕድል የፈጠረ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ነው።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ1 ሺህ 200 በላይ ወረዳዎችን በማዳረስ ያከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የዜጎች ተሳትፎ የተረጋገጠበት ነው።

ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተፈናቃዮች እንዲሁም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት እና የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ሳይቀሩ በምክክሩ እንዲሳተፉ መደረጉ የሂደቱን አካታችነት እና ህዝባዊ መሠረት ያጎላዋል።

በአሁኑ ወቅት በመዲናችን አዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው።

ከ4 ሺህ በላይ በሕዝብ የተመረጡ ተወካዮች በራሳቸው ባህልና ቋንቋ፣ በነፃነት ስጋታቸውን እና ምኞታቸውን እያንፀባረቁበት ይገኛሉ።

ይህ ጉባኤ ስብሰባ ብቻ ሳይሆን፣ የተዛባውን የሀገራችንን ትርክት አርሞ፣ የተበታተነውን ሰፍቶ አንድ ላይ የሚያያይዝ የትውልዶች ድልድይ ነው።

መላ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው አቅም፣ በሰከነ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ የምክክር ባህል ለመፍታት ያሳዩት ይህ ቁርጠኝነት ጠንካራ መሠረት ያለን ሀገረ-መንግሥት እንድንሆን ያስችለናል።

ጉባኤው የሚያቀርባቸው የፖሊሲ አማራጮች እና የሚያስቀምጣቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች፣ ለቀጣናው ሰላም ብቻ ሳይሆን በውስብስብ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ለሚገኙ የዓለም ሀገራት ጭምር ትልቅ ተምሳሌት እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

በሰለሞን ገዳ
#ethiopia #nationaldialogue #nationalconsensus #peacebuilding #ebc

11 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.