Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ካውንስ ዋና ጸሐፊ ቄስ ጀሪ ፒላይ በአማራ ክልል በአምልኮ ቦታዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እንዲሁም የሲቪሎችን መገደል እና መቁሰል "እጅግ የሚረብሽ እና ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው" ሲሉ በጽኑ አውግዘዋል። ዋና ጸሐፊው ዛሬ ባወጡት መግለጫ፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሲቪሎች በፍጹም ኢላማ ሊደረጉ ወይም በወታደራዊ ዘመቻዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ሊገቡ እንደማይገባ በማሳሰብ፣ በአማራ ክልል በሲቪል ማኅበረሰብ እና በሃይማኖት ተቋማት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

ካውንስሉ ባወጣው መግለጫ በጥቃቱ ዙሪያ አስቸኳይ፣ ተዓማኒ፣ ግልጽ እና ገለልተኛ የሆነ ምርመራ እንዲካሄድና ይህንን ድርጊት የፈጸሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ጥሪ አቅርቧል። በተጨማሪም ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን እንዲያከብሩ እንዲሁም ሲቪሎችንና የሃይማኖት ተቋማትን የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲወጡ ዋና ጸሐፊው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የጥቃት አዙሪቱን እንዲያስቆሙ፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ መከራ የሚያስከትሉ ጥቃቶችን እንዲገቱ እና አሁን ላለው ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉም አበክረው ጠይቀዋል።

መግለጫው በማጠቃለያው ለተጎጂዎች ያለውን አጋርነት በመግለጽ፣ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች ጥልቅ ሀዘናቸውን ገልጸው ለቆሰሉት ፈውስን ተመኝተዋል። እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በክርስቲያናዊ አንድነት እንደሚቆሙ በማረጋገጥ፣ የሰላም አምላክ ሀዘንተኞችን እንዲያጽናና፣ ንጹሃንን እንዲጠብቅና ኢትዮጵያንም ወደ ፍትህ፣ ዕርቅ እና ዘላቂ ሰላም እንዲመራት መልካም ምኞታቸውን እና ጸሎታቸውን አስተላልፈዋል።

10 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.