የአገልግሎት በደልን ያከሰመው ቴክኖሎጂ
*********************
(የዕለቱ መልዕክት)
ለዘመናት የኢትዮጵያ መንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ የዜጎችን ትዕግሥት የሚፈትን፣ ጉልበት እና ጊዜን የሚበላ የ"ዶሴ ዘመን" እስረኛ ሆኖ ቆይቷል።
ዜጎች ወረቀት ታቅፈው ረጅም ሰልፍ ተሰልፈው ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላው ሲንከራተቱ፣ "ፋይል ጠፍቷል" በሚል ሰበብ ለሙስና፣ ለእጅ መንሻ እንዲሁም ለተለያየ እንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸው የአደባባይ ምስጢር ብቻ ሳይሆን የሀገር ሕመም ነበር።
ይህ ማነቆ ግለሰባዊ እንግልት ብቻ ሳይሆን በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን መተማመን የሚሸረሽር፣ መልካም አስተዳደርን የሚያቀጭጭ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ቀውስ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
አሁን ግን ይህን አድካሚ የወረቀት ቢሮክራሲ ታሪክ የሚያደርግ፣ የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥ ባህል ከመሰረቱ የሚቀይር "መሶብ" የተሰኘ ሀገር በቀል የዲጂታል ሥርዓት የብርሃን ጮራ ፈንጥቋል።
«መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ ተቋማትን አገልግሎቶች በአንድ ማዕድ በማሰባሰብ ዜጎች ሁሉንም ጉዳዮቻቸውን በአንድ መስኮት በቀላሉ እንዲያጠናቅቁ የሚያስችል ሥርዓት ነው።
ይህ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን ከማቀናጀት የላቀ ጥልቅ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ትርጉም አለው።
አንድ ጉዳይ መቼ እንደገባ እና በማን እጅ እንዳለ በግልጽ የሚያሳይ በመሆኑ፣ ለሙስና የሚደረጉ ድብቅ ድርድሮችን ከመሰረቱ ያመክናል።
አገልግሎት ፈላጊው ከሚስተናገድበት አካል ጋር የሚኖረውን ኢ-መደበኛ የጥቅም መስተጋብር በመቁረጥ መልካም አስተዳደርን በተግባር ያረጋግጣል።
ይህ ደግሞ የተንዛዙ አሠራሮች የሚፈጥሩትን የዜጎች ቅሬታ በማስወገድ፣ በመንግሥት ሥርዓት ላይ ያላቸውን አመኔታ እና እርካታ በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል፤ ፖለቲካዊ መረጋጋትንም ያጠናክራል።
በኢኮኖሚው ዘርፍም ቢሆን የመሶብ ትሩፋት እጅግ የጎላ ነው። የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር እውን የሚሆነው በመሰል ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ነው። ዜጎች ወረቀት በማሳደድ የሚያጠፉት ወርቃማ ጊዜ ወደ ማምረቻነት ሲቀየር ሀገራዊ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ያድጋል። ሥራ ፈጣሪዎች እና ነጋዴዎች ፈጣን አገልግሎት ሲያገኙ፣ የንግድ እንቅስቃሴው ይፋጠናል፤ የሀብት ብክነትም ይቆማል።
ማኅበራዊ ፍትሕን ከማስፈን አኳያም፣ ሁሉም ዜጋ በቴክኖሎጂ ታግዞ ያለ አድልዎ እኩል፣ ቀልጣፋ እና ግልጽ አገልግሎት ማግኘቱ ዴሞክራሲያዊ እኩልነትን እና ማኅበራዊ መስተጋብርን ያጠናክራል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጅማሬውን ያደረገው ይህ የተቀናጀ የአገልግሎት ሥርዓት፣ በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ከ100 በላይ ማዕከላትን በመክፈት ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ከዚህም አልፎ ተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎቶች እና ዜጎች ባሉበት ሆነው አገልግሎት የሚያገኙበት የተቀናጀ የዲጂታል ሞባይል መተግበሪያ ወደ ሥራ መግባቱ ተደራሽነትን ይበልጥ አስፍቶታል።
ይህ አበረታች ጅማሬ በተጠና ስትራቴጂ እየተመራ ሲሆን፣ ከ2019 እስከ 2021 ዓ.ም በሚተገበረው አዲስ ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት በሁሉም ወረዳዎች ተደራሽ ለማድረግ፣ ተቋማዊ አሠራሩን ለማዘመንና ጥራቱን ለማሳደግ ትልቅ ራዕይ ተሰንቋል።
በአጠቃላይ «መሶብ» የዶሴ ዘመንን ሸኝቶ የዲጂታል ዘመንን ያበሰረ፣ መንግሥት ለሰው ተኮር አገልግሎት የሰጠው ትኩረት ማረጋገጫ ነው። ይህ ሥርዓት የሀገራችንን ፖለቲካዊ ጤናማነት፣ ማህበራዊ ፍትሕ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያፋጥን ሞተር ነው።
በመሆኑም ይህ ታሪካዊ የአገልግሎት አሰጣጥ እጥፋት ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ፣ የጀመርነው የዲጂታል ብርሃን እንዳይደበዝዝ እንዲሁም ለሥርዓቱ ቀጣይነት ጠንካራ የሳይበር ደኅንነት ጥበቃ ማድረግ ይገባል።
እያንዳንዱ ዜጋ፣ ማኅበረሰብ እና ባለድርሻ አካል ይህን ሥርዓት በባለቤትነት ሊጠብቀው፣ ከአሠራር ግድፈቶች ሊታደገው፣ ባህል አድርጎ ሊወስደው እና ይበልጥ ሊያጎለብተው ግድ ይላል!
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

13 days ago