Logo
Getu Temesgen
"ዘርፉ ሙሉ በሙሉ የህዝብ አመኔታ እንዲያገኝ ነው የምንሰራው"
#ethiopia | በኢትዮጵያ የሪል ስቴት ዘርፍ የህዝብን አመኔታ በመገንባት፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ሁለት ስትራቴጂያዊ የመግባቢያ ሰነዶች ዛሬ በይፋ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር (EREDA) እና ዶክሳ ቢዝነስ ትሬዲንግ ሲሆኑ፣ ትብብሩ በዘርፉ የተከማቹ የፖሊሲ፣ የፋይናንስ፣ የኢንቨስትመንት እና የትስስር ክፍተቶችን በመቅረፍ ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዝ ተገልጿል።

በስምምነቱ መሠረት የሪል ስቴት አልሚዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የፖሊሲ አውጪዎችና የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች በአንድ መድረክ በማገናኘት እስካሁን በዘርፉ የታየውን የተቆራረጠ የሥራ አሰራር ለማስቀረት ይሰራል።

እንደ መነሻ ሁለቱ ተቋማት በቅርቡ በሚካሄዱ ዓመታዊ የሪል ስቴት ጉባኤዎችና የኤክስፖ መድረኮች ላይ በጋራ በመሳተፍ የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ተቋማቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ ትብብሩ በግልጽ የኃላፊነት ክፍፍል፣ የሥራ ጊዜ ሰሌዳ እና የሚጠበቁ ውጤቶች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ዘርፉን በሳይንሳዊና በተጠያቂነት መርህ ለመምራት ያግዛል ብለዋል።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ሚካኤል ጆርጅ፣ "ዘርፉ ሙሉ በሙሉ የህዝብ አመኔታ እንዲያገኝ ነው የምንሰራው" ሲሉ ገልጸዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ሙያዊ መመዘኛዎችን ማስከበር፣ ግልጽነትን ማጠናከር እና የባለድርሻ አካላትን ትብብር ማሳደግ የማህበሩ ዋና ትኩረቶች ናቸው።

ዶክሳ ቢዝነስ ትሬዲንግ በበኩሉ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ አዳዲስ የንግድ ትስስሮችን በመፍጠር እና የኢትዮጵያን የሪል ስቴት ዘርፍ ከአህጉራዊ ገበያ ጋር በማስተሳሰር የድርሻውን እንደሚወጣ ተገልጿል።

ተፈራራሚዎቹ እንደገለጹት፣ ይህ ስምምነት በዘርፉ የሚታዩትን የመሠረተ ልማት፣ የፋይናንስ አቅርቦትና የኢንቨስትመንት ችግሮች ለመቅረፍ ወሳኝ መሠረት እንደሚሆን እና የኢትዮጵያን የቤት ልማት ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፍ የንግድ ትስስሮች ጋር ለማቀናጀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

ሔኖክ ወ/ገብርኤል

ፎቶ፦ ከበደ መክብብ
#ethiopia #getutemesgen #getunews

15 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.