Logo
EBC
መሶብ የጊዜና የሀብት ብክነትን አስቀርቶልናል - የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች
******************

የመንግሥት አገልግሎት እና የአስተዳደር ሪፎርም ውጤታማ እንዲሆን በከተሞች የተጀመረው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ነባራዊ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ አይነተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።

ይህ ዘመናዊ አሠራር በተለይም ከዚህ ቀደም በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበረውን ጥርጣሬ በመቀነስ ዜጎች ያጋጥማቸው የነበረውን የጊዜ እና የሀብት ብክነት በከፍተኛ ደረጃ ማስቀረት ችሏል።

የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ማስተሳሰሩ ከዚህ ቀደም ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላ ቢሮ ለመንከራተት ይዳርግ የነበረውን ከፍተኛ እንግልት አስቀርቶላቸዋል።

የማዕከሉ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ መሆናቸው፣ ማኅበረሰቡ ቴክኖሎጂን በአግባቡና በብቃት እንዲጠቀም አዲስ መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተክለአብ ቡሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥት ነባራዊ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ማዕቀፎችን ቀርጾ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የቦንጋ መሶብ አንድ ማዕከልም የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን በማዘመን፣ ለዜጎች ምቹና ቀልጣፋ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተካሄደ የሚገኘውን አገራዊ ጥረት የሚያግዝ ተጨማሪ ትልቅ አቅም መሆኑን ከንቲባው አብራርተዋል።

አሁን ላይ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ይህ የቦንጋ መሶብ አንድ ማዕከል፤ 3 የፌዴራል ተቋማትን ጨምሮ 8 የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በአንድ ጥላ ሥር ያካተተ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 44 ልዩ ልዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለአካባቢው ነዋሪዎች በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

በሰለሞን ባረና

18 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.