Logo
EBC
ማዕድ ከማድመቅ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እስከመሆን የዘለቀው ቡናችን
******************

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር እና መለያችን የሆነው አረንጓዴው ወርቅ ዛሬ ላይ ከሀገር ውስጥ የፍጆታ ገበያ አልፎ የሀገራችንን ማክሮ ኢኮኖሚ በውጭ ምንዛሬ በመደገፍ ረገድ ታሪካዊ የተባለለትን ስኬት እያስመዘገበ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ እንደመሆኗ ምርቱ በባሕላችን ውስጥ ጥልቅ ሥር አለው። ሀገራችን በዓመት ከምታመርተው አጠቃላይ የቡና ምርት ውስጥ ግማሽ ያህሉን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ታውላለች።

ይህን ከፍተኛ የሕዝብ ፍላጎት እያሟላችም በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ በመሆን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ችላለች።

በተለይም በ2018 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ከ600 ሺህ ቶን በላይ ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ 3.1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማስገኘት መቻሏ ታሪካዊ ክንውን ሆኗል።

ይህ የገቢ መጠን በ2014 ዓ.ም ተመዝግቦ ከነበረው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ማደጉን ያሳያል።

የዚህ አስደናቂ ስኬት መሠረት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ የፖሊሲ ትኩረት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደጋግመው ገልጸዋል።

ሀገራዊ የሪፎርም ሥራው ከመጀመሩ በፊት ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ በዓመት ታገኝ የነበረው ገቢ 700 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብቻ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ መንግሥት የሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የ'አረቢካ' ቡና ወደ ውጭ በመላክ ሦስተኛዋ ሀገር እንድትሆን እንዳስቻላት አስገንዝበዋል።

አክለውም እያደገ የመጣው የሕዝብ ቁጥር እና የቡና ፍጆታ ምርቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዳለው እንደሚያሳይ እና ይህም በዘርፉ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣቱን አስረድተዋል።

ይህ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ስኬት በተከታታይ በተተገበሩ ስር ነቀል መዋቅራዊ ማሻሻያዎች የመጣ ውጤት ነው።

ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር፣ በመሀል ከ40 በመቶ በላይ የቡና ዋጋ ይወስዱ የነበሩ ደላሎችን በማስወገድ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ወደ ውጭ የሚልክበት "የቀጥታ ግብይት ትስስር" መፈጠሩ ነው።

በዚህም ምክንያት የአርሶ አደሩ የትርፍ ድርሻ ከ40 በመቶ ወደ 80 እና 90 በመቶ ከፍ ሊል ችሏል።

በተጨማሪም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን በመትከል፣ ያረጁ ዛፎችን በመጎንደል እንዲሁም ከቀረጥ ነፃ በገቡ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት የምርት መጠኑን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል።

በዚህም የይርጋጨፌ፣ የሲዳማ፣ የሀረር፣ የጂማ እና የሌሎችም አካባቢዎች መለያ የሆነው አረንጓዴው ወርቃችን ታሪካዊውን የውጭ ምንዛሬ ግብ ማሳካት ችሏል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ይህንን ስኬት ያስመዘገበችው ተፈጥሮን ሳይጎዳ፣ ከደን ጋር በተዋሃደ የጥላ ሥር የቡና እርሻ ሥርዓት (Shade-grown coffee) መሆኑ፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ለአየር ንብረት ለውጥ ተቆርቋሪነቷን በማሳየት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ አኩሪ ገጽታዋ ነው።

በለሚ ታደሰ
#ethiopia #ebc #ethiopiancoffee #macroeconomy #coffeeexport #greenlegacy

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.