Logo
EBC
ሰው በመሆን የምትጸና ሀገር፡ የመረዳዳት ባህላችን ትሩፋት
***************
(የዕለቱ መልዕክት)

የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት ባህል ከበጎ አድራጎትነትም በላይ ጥልቅ የህይወት ፍልስፍናችን እና የህልውናችን መሰረት ነው።
ሰብዓዊነት የሚጀምረው ከራስ አልፎ ለሌላው መትረፍ ሲቻል ሲሆን አንድ ሰው የሌላውን እንባ ሲያብስና የወደቀውን ሲያነሳ የራሱን ሰብዓዊ ክብር ወደ ላቀ የሞራል ጣሪያ ከፍ ያደርጋል።

ዕድር፣ ዕቁብ፣ ደቦ እና ማህበር በሀገራችን ማህበራዊ ስያሜዎች ብቻ ሳይሆኑ ዘመናዊው ዓለም ዛሬ 'ማህበራዊ ዋስትና' ብሎ የደረሰበትን ጽንሰ-ሀሳብ እኛ ቀድመን በአገር በቀል ጥበብ የገነባንባቸው ጠንካራ መዋቅሮቻችን ናቸው።

የጎረቤታችን ችግር የኛም ጭምር መሆኑን አምነን፣ በሀዘን አብሮ በማልቀስና ላዘመመ ቤት በጋራ በመቆም የምንገልጸው ማንነት የህዝቦቻችንን ጥብቅ ትስስር ያሳያል።

በሁሉም አካባቢ ይህ እሴት ጎልቶ የሚታይ ሲታይ የታረዘውን ማልበስና ማዕዱን ለሌለው ማጋራት የህዝባችን ዋነኛ መገለጫ ሆኖ እናገኘዋለን።

ይህንን የህዝብ እሴት ወደ መንግስታዊ መሪነት በማሸጋገር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች የዚሁ አብሮነታችን ዘመናዊ መገለጫዎች ናቸው።

በተለይም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናትን በትምህርት ገበታ ላይ ያቆየው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር፣ እናቶችና አባቶችን ከፈረሰ ጎጆ ወደ ምቹ ማረፊያ ያሸጋገረው የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት እንዲሁም ወጣቱ ትውልድ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚያደርገው የደም ልገሳና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የሰው ተኮር ልማቱ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው።

እነዚህ ተግባራት መረዳዳትን ከተቋማዊ ኃላፊነት ጋር ያቆራኙ ናቸው። ይህ የሚያሳየው እውነተኛ ልማት ትርጉም የሚኖረው ግዙፍ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ከመገንባት ባለፈ ሰውን ማዕከል ሲያደርግ፣ የዜጎችን ህይወት በቀጥታ ሲነካ እና የወደቁትን ሲያነሳ መሆኑን ነው።

በመሆኑም መደጋገፍና አብሮነት ጊዜያዊ ስሜቶች ሳይሆኑ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣትና ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት የሚያስፈልጉን ዋነኛ መሰረቶቻችን ናቸው።

አንዱ የሌላውን ችግር በመካፈል፣ የብሔርና የሃይማኖት ድንበሮችን ተሻግረን ሰው በመሆናችን ብቻ ስንተሳሰር የሀገራችን አንድነት ይበልጥ የጠነከረ ይሆናል።

መረዳዳት ልዩነቶችን የሚያከስም፣ ግጭቶችን የሚያረክስና ብሔራዊ ማንነታችንን የሚያጸና ታላቅ ሀብታችን ነው። ይህን አኩሪ የሞራል ከፍታ ለትውልድ እያወረስን በሰብዓዊነት ጥላ ስር ጠንካራና አንገቷን ቀና የምታደርግ ህብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

22 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.