Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት ዋና ምክንያት የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ ሳይሆን የሀገሪቱ የውስጥ የፖለቲካ መከፋፈል መሆኑን በድጋሚ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ዛሬ በአዲስ አበባ በተከፈተው «የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ» መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

በንግግራቸው ኢትዮጵያ የባህር በርን «ለሺህ ዓመታት አስተዳድራ፣ በባለቤትነት ይዛ እና ተጠቅማበት እንደነበር» አስታውሰው፣ አሁን ላለችበት የባህር በር አልባነት ሁኔታ ተጠያቂው «የውጭ ኃይሎች ሳይሆን የእኛ የውስጥ ድክመት ነው» ብለዋል። «በዚህ ጉዞ ውስጥ በራሳችን ውስጣዊ ድክመት እና በሌሎች ዕድለኝነት የባህር በራችንን አጥተናል» ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያን በቋሚነት ከብሔራዊ ጥቅሟ ሊያግዳት የሚችል የውጭ ኃይል እንዳልነበረ አክለዋል።

በንግግራቸው አንዳንድ የውጭ ኃይሎችን «በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እንደሚንሳፈፉ አሞራዎች» የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ በምትገነባበት ጊዜ እንደማይገኙና በተቃራኒው በውስጥ ግጭት ስትታመስ ግን ተገኝተው ድጋፍና ፕሮፓጋንዳ እንደሚያቀርቡ ከሰዋል። «ለእነዚህ አሞራዎች መልእክቴ ይህ ነው፤ ከብቱን የምንገዛው እኛ፣ የምንቆራርጠው እኛ ነን፤ እኛ በፈቃዳችን ካልሰጠን በቀር ማንም አሞራ ከጠረጴዛችን ላይ በኃይል ሊወስድ አይችልም» ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ትብብር ለመፍጠር ሁልጊዜም ዝግጁ እንደሆነች ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን አንድነት ያላት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ትለቃለች ተብሎ መጠበቅ «ከንቱ ተስፋ» እንደሆነ አስምረውበታል።
በሌላ በኩል፣ ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየባትን አለመግባባቶችን በኃይል የመፍታት ባህል በመቀየር በሰላማዊ ውይይት የመፍታት ልምድ የምታዳብርበት እንደሆነ ጠቁመዋል። «የፖለቲካችን በጠንካራ ቃል ይጀምራል፣ በኃይል እርምጃ ያልቃል፤ ይህንን ስብራት በአንዴ ልንፈውሰው ይገባል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የምክክር ባህልን ማዳበር የሀገሪቱን አንድነት ከማጠናከሩም በላይ የውጭ ጣልቃ-ገብነትን እንደሚቀንስ ገልጸዋል።

ንግግራቸውን ሲያገባድዱም በጉባኤው ለተሳተፉት ከአራት ሺህ በላይ ታዳሚዎች ባስተላለፉት መልእክት፣ «ስለ ምን ጉዳይ ብንከራከርም በውይይት መፍታት እንችላለን፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለውጭ ኃይሎች የምታሳልፍበት አደገኛ ታሪካዊ አረም ላለመሆን ሁላችንም መጣር አለብን» በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

23 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.