Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የኮሎምቢያው ተጨዋች በአገሩ በደረሰበት የግድያ ዛቻ ለመደበቅ ተገደደ፡፡ ጉዳዩ የሚጀምረው ባለፈው ሳምንት ጁላይ 8 በቫንኮቨር ስታዲየም ኮሎምቢያና ስዊዘርላንድ ካደረጉት የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ነው፡፡ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለምንም ግብ በመጠናቀቁ ወደተጨማሪ ሰአት ይሸጋገራሉ፡፡ ተጨማሪው ሰአትም ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት የኮሎምቢያው ጃሚንተን ካምፓዝ ከስዊዘርላንድ ግብ ጠባቂ ጋር ብቻ የተገናኘበት አጋጣሚ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ጎል ማስቆጠር ሳይችል መቅረቱ ይታወሳል፡፡

በመሆኑም ወደፍፁም ቅጣት ምት ተሸጋግረው ኮሎምቢያ 4 ለ 3 በሆነ ውጤት ተሸንፋ ወደሩብ ፍፃሜው ማለፍ ተስኗታል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱን ከሳቱት የኮሎምቢያ ሶስት ተጨዋቾች መካከል ደግሞ ካምፓዝ አንዱ ነው፡፡ ለአርጀንቲናው ሮዛሪዮ ሴንትራል ክለብ የሚጫወተው ይህ የ26 አመቱ ተጨዋች ከዚህ ሽንፈት በኋላ ወደአገሩ አልተመለሰም፡፡ ምክንያቱም የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቹ አሉታዊ አስተያየቶችና በግድያ ዛቻዎች ተጥለቅልቀዋል፡፡

የማህበራዊ ሚዲያዎቹን አስተያየት መስጫ የዘጋው ይህ ተጨዋች ከቡድን አጋሮቹ ጋር ወደኮሎምቢያ ከመሄድ በመቆጠብ መደበቅን መርጧል፡፡ ካምፓዝ በኢንስታግራም ገፁ ላይ ለአገሩ ደጋፊዎች ባስተላለፈው የይቅርታ መልእክት ‹‹ሁላችንም ተስፋ ያደረግነውን ልሰጣችሁ ባለመቻሌ አዝናለሁ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ማሊያ ፍቅር፣ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት አሳንሼበት እንደማላውቅ እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በሜዳ ላይ ያለኝን ሁሉ ሰጥቻለሁ፡፡ ይህንን ደግሞ ለአገሬ ሺህ ጊዜ አደርገዋለሁ፡፡›› ያለ ሲሆን አያይዞም ፍፁም ቅጣት ምት በሳተበት ወቅት ፊቱን በእጁ ሸፍኖ ሲቆጭ የሚያሳየውን ፎቶግራፍ ለጥፏል፡፡ እግር ኳስ አስቸጋሪ በመሆኑ ብስጭትና ሀዘን እንደሚያስከትል ገልፆም ይህንን ወደጥላቻ መቀየር እንደማያስፈልግ አሳስቧል፡፡

የኮሎምቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ በዚህ አማካኝ ተጨዋች ላይ የተደረገው የግድያ ዛቻ እንዲመረመር አሳስቧል፡፡ ፌዴሬሽኑ ጨምሮም አቃቤ ህግ በአስቸኳይ ይህንን ዛቻ ያደረሱትን ግለሰቦች መርምሮ ለፍርድ እንዲያቀርብም ጠይቋል፡፡ እንዲሁም ‹‹የካምፓዝን ህይወትና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ዛቻዎችን ፈፅሞ እናወግዛለን›› ያለው መግለጫው ኮሎምቢያን ወክለው በአለም ዋንጫው ላይ የተሰለፉ ተጨዋቾች በሙሉ ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅር፣ ቁርጠኝነትና ታማኝነት ማሳየታቸውን ገልጿል፡፡

ይህ ክስተት በኮሎምቢያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የተፈጠረውን ጥቁር ምእራፍ የሚያስታውስ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 በአሜሪካ በተደረገው የአለም ዋንጫ ወቅት ኮሎምቢያ በአዘጋጇ አገር 2 ለ 1 በተሸነፈችበት ወቅት የኮሎምቢያው ተከላካይ አንድሬስ ስኮባር በራሱ ጎል ላይ ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ብሄራዊ ቡድኑ ወደአገሩ ከተመለሰ በኋላ ኢስኮባር በጠራራ ፀሀይ መገደሉ አይዘነጋም፡፡ የኮሎምቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዚህ መግለጫው ‹‹እግር ኳስ ለአንድነት፣ ለአክብሮትና ለተስፋ ክፍተት መስጠት ይኖርበታል እንጂ የጥላቻ፣ የማስፈራራትና የአመፅ መድረክ መሆን የለበትም›› ሲል የገለፀውም ለዚህ ነው፡፡

25 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.