Logo
FBC
የመዳረሻዎች ዕድገት ኢትዮጵያን በሰማይ የማገናኘት ስኬት

በየትኛውም ሀገር የአቪዬሽን ዘርፍ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ትስስር ዋነኛ የጀርባ አጥንት ነው።

ኢትዮጵያ ሰፊ መልክዓ-ምድር፣ ተራራማ አቀማመጥና እጅግ በርካታ ሕዝብ ያላት ሀገር በመሆንዋ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የአየር ትራንስፖርት አማራጭ መኖሩ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ በተለይም በመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን በማስፋፋትና መሰረተ ልማቶችን በማዘመን ረገድ ታሪካዊ የተባለ ዕድገት አስመዝግቧል።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ በረራዎች በጥቂት ዋና ዋና ከተሞችና የቱሪስት መስመሮች ማለትም እንደ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደርና ባሕር ዳር ላይ ብቻ የተገደቡ ነበሩ።

ይሁን እንጂ አየር መንገዱ ባወጣው ራዕይ 2035 ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሠረት፣ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ችሏል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መደበኛ የመንገደኞች በረራ የሚያደርግባቸው የሀገር ውስጥ ከተሞች ቁጥር 26 ደርሷል።

በተለይም በቅርቡ የተገነቡትና ሥራ የጀመሩት አራት አዳዲስ የክልል አውሮፕላን ማረፊያዎች የዘርፉን ተደራሽነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረውታል።

እነዚህ አዳዲስ ማረፊያዎች ቀደም ሲል በመንገድ መሰረተ ልማት እጥረትና በረጅም ሰዓት ጉዞ ምክንያት ከአዲስ አበባና ከሌሎች ማዕከላት ተለይተው የቆዩ አካባቢዎችን በቀጥታ በሰዓታት ልዩነት ማገናኘት ችለዋል።

የመዳረሻዎች ዕድገት የመጣው አዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎችን በመገንባት ብቻ አይደለም፤ ነባር የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎችን በከፍተኛ በጀት የማዘመን ሥራ ተከናውኗል።

እንደ ጅማ፣ ሰመራ፣ ጋምቤላና አሶሳ ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ዘመናዊ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናሎች ተገንብተውላቸዋል።

ይህም በአንድ ጊዜ በርካታ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅማቸውን አሳድጎታል።

በርካታ የሀገር ውስጥ ማረፊያዎች ቀደም ሲል ትናንሽ አውሮፕላኖችን ብቻ ያስተናግዱ ነበር።

አሁን ግን ማኮብኮቢያዎቻቸው በዘርፉ የጥራት ደረጃ በመታደሳቸው እንደ Boeing 737 ያሉ መካከለኛና ትላልቅ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን በደኅንነት ማሳረፍ የሚያስችል አቅም አግኝተዋል።

የሀገር ውስጥ የበረራ ትስስር መዘርጋት ለሀገሪቱ በርካታ አዎንታዊ ውጤቶችን አስገኝቷል።

የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ አውሮፕላን መዳረሻዎች ዕድገት የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን ትልቅ ሥራ ነው።

የመንገደኞች ቁጥር በየዓመቱ እያደገ መምጣቱና የሕዝቡ የአየር ጉዞ ፍላጎት መጨመር፣ አየር መንገዱ ወደፊትም ተጨማሪ ከተሞችን ወደ በረራ መርሃ-ግብሩ እንዲያስገባ ግድ ይለዋል።

ይህ በሰማይ ላይ የተዘረጋው ጠንካራ ሰንሰለት ኢትዮጵያን ይበልጥ አንድ ለማድረግና የሕዝቦቿን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ከፍታ ለማውጣት ያለው ሚና የጎላ ነው።

26 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.