Logo
FastMereja
አንጋፋዋ ድምፃዊት ራሄል ዮሐንስ

ከግራውንድ ሆስተስ እስከ ታዋቂ ድምፃዊነት ከመቀጠር ወደ መቅጠር ፣ ከሰራተኝነት ወደ ጀኔራል ማናጀርነት ተሸጋግራም አገልግላለች፡፡ ራስ ሆቴል ፣ ጊዮን ሆቴል ፣ አርጀንቲና ፣ ታንዛኒያ እና ፊሊፕስ ኢምባሲ ፣ ሸበሌ ሆቴል ፣ ሂልተን ሆቴል ፎርሺፕ ትራቭል ፣ አነስ ያለች ሆቴል (በግሏ ከፍታ) ሰርታለች፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ቀስ በቀስ ወደ ድምፃዊነቱ አምርት በርካታ ስራዎቿን ለአድናቂዎቿ ያደረሰችው። የወይን ስፔሳሊስቷ አርቲስት ራሄል ዮሀንስ።

መዲናችን አዲስ አበባ ካዛንቺስ ግቢ ገብርኤል አካባቢ ሚያዚያ 27 ቀን 1939 ዓ.ም ነው የተወለደችው፡፡ ለቤተሰቦቿ የበኩር ልጅ የሆነችው ራሄል ዮሀንስ ከታናሽ ወንድሟ ድምፃዊ ሰይፉ ዮሀንስ ጋር የቄስ ትምህርትን እስከ ዳዊት ቆጥራለች፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ ሰይፉ ዮሀንስን “ሀና ሀና” በተሰኘ ስራው ታስታውሱታላችሁ፡፡

ራሄል የ 1ኛ ደረጃ ትምህርቷን በአስፋ ወሰን ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡ ወደ ሆቴል ሙያ ያዘነበለችው ራሄል ዮሀንስ በራስ ሆቴል ለ 3ወር አጠቃላይ የመስተንግዶ ስነ ስርዓት ተምራለች፡፡ በመቀጠልም በምርጫዋ በጊዮን ሆቴል የወይን መስተንግዶ ትምህርትን ለሁለት አመታት ተከታትላ ዲፕሎማ አግኝታለች፡፡

ድምፃዊት ራሔል በሆቴል ቆይታዋም ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ባለስልጣናትን እና የአፍሪካ እንዲሁም ሌሎች ሀገራት መሪዎችን አስተናግዳለች፡፡ እነ ጋማል አብዱል ናስር ፣ ሴኩ ቱሬ ፣ ክዋሚ ንኩርማ እና ሌሎችንም፡፡ ገና በልጅነቷ ሆስተስ (የበረራ አስተናጋጅ) የመሆን ህልም የነበራት በኋላ ግን ግራውንድ ሆስተስ (የሆቴል አስተናጋጅ) የሆነች ራሄል ዮሀንስ በሆቴሎቹ ባገለገለችባቸው ጊዜያት ውስጥ ከ 80 እስከ 200 ብር ይከፈላት ነበር፡፡ ቲፕ ተሰብበስቦ ለሁላችንም እንደ የደረጃችን በፐርሰንት ይከፈለን ነበርና ከደሞዛችን ይልቅ ይኸ ሻል ያለ ነበር ትላለች ራሔል ያንን ጊዜ ስታስታውሰው፡፡

አንድ ቀን ድምፃዊ ከተማ መኮንን እና ሌሎች አንጋፋ ሰዎች በቤቷ ተገኝተው ምግብ ከተመገቡ በኋላ በጋሽ ከተማ አጋፋሪነት ጨዋታው ደራ፡፡ እሱ ማሲንቆ ሲጫወት እሷም ማንጎራጎሯን ቀጠለች በድምጧ የተደነቁት ሰዎች ምግብ ቤቱን ትታ ዘፋኝ አንድትሆን ይገፋፏታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ወደ ድምፃዊነት ሙያ ገባች፡፡

ከዚያም ከጥቂት አመታት በኋላ በ 70ዎቹ (1973/74ዓ.ም) የመጀመሪያ ስራዋን “አንቺ ባለድሪ” የተሰኘ አለበም ከሻምበል በላይነህ ጋር አወጣች፡፡ በወቅቱም ለዚህ ስራ አምባሳል ሙዚቃ ቤት 10,000 ብር ከፍሏታል፡፡ በዚህ ካሴት ውስጥ በግጥም – ይልማ ገብረአብ እና በዜማ – አበበ መለሰ ተሳትፈዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በ 1983 ዓ.ም ከታዋቂዎቹ የሀገር ባህል ተጨዋቾች ከባህሩ ቀኜ እና ከይርጋ ዱባለ ጋር የሰራቻቸው ዘፈኖችም በህዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ናቸው፡፡

አራዳ ፣ ትዝታ ፣ ምኒልክ እና ሀገሬ ኢትዮጵያ ያሉት ደግሞ በግሏ ከሰራቻቸው ተወዳጅ ዜማዎቿ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ አርቲስት ራሄል ዮሀንስ ሙዚቃ እስካቆመችበት ጊዜ ድረስ ወደ 13 የሚጠጉ አልበሞችን ሰርታለች፡፡ በነገራችን ላይ ድምፃዊት ራሄል ዮሀንስ ከዘፋኝነቷ ባሻገር የዜማ ደራሲም ጭምር ናት፡፡

ለአብነትም ምኒልክ ፣ ጀግናው ሰራዊት ፣ እንደ እየሩሳሌም (የአስናቀች ወርቁን በድጋሚ በራሷ ዜማ የሰራችው) እና ሌሎችንም ዜማ ደርሳለች፡፡ የመጨረሻ ስራዋ “ዘናበል” የሚል አልበሟ ሲሆን በያሬድ ተፈራ የተቀናበረ አልበም ነበር፡፡

በአንድ ወቅት እንዲህ ተብሎም ተገጥሞላት ነበር፡-

“አዝማሪ ይሏታል ራሄል ሆዴን
አዝማሪ ይሏታል ጭንቄ ራሄልን
ልጆች ለማሳደግ ያደረገችውን፡፡” በማለት ……..

የሁለት ወንድ እና አራት ሴት ልጆችን ያፈራቸው ድምፃዊ ራሔል አሁን ላይ አያት የሆነችው ራሄል በርከት ያሉ የልጅ ልጆችንም አይታለች፡፡

Ⓒ EthiopiaAnything

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.