Logo
Zehabesha
*ከመረጥነው የህይወት አቅጣጫ ይልቅ ያልመረጥነው ለምን የተሻለ መስሎ ይታየን ይሆን?*

ሶረን ኬርኬጋርድ የሚባል የዴኒሽ ፈላስፋ ትዝብቱን ሲያስቀምጥ እንዲህ ይላል "ማንኛውም ወሳኝ የሆነ የህይወት ውሳኔ የራሱ የሆነ ትርፍና ኪሳራ ይዞ ይመጣል"። ውሳኔያችን ምንም ይሁን በአንድ በኩል የእድል በር ሲከፍትልን በሌላው በኩል ግን በዚህ ውሳኔያችን ምክንያት እንደሚዘጋ ሌላ በር መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ብዙ ሰዎች የሆነ ብቸኛ ውሳኔ በራሱ ደስተኛ የሚያረጋቸው ይመስል ፍፁማዊ የሆነ ውሳኔ ለሠወሰን ህይወታቸውን ሙሉ ሲባዝኑ እናያለን። እውነታው ግን እያንዳንዱ የህይወት ውሳኔ እርካታን ብቻ ሳይሆን ቁጭትም ይኖሩታል።

ካሉት አማራጮች ውስጥ አንዱን መንገድ በመረጥን ሰአት ሌለኛውን መንገድ ተሰናብተን እንሄዳለን። በማንኛውም ምርጫችን የምናገኘው በረከት ሌለኛውን በረከት መስዋት አድርገን ነው።

እዚህ ላይ ችግሩ ውሳኔያችን ራሱ አይደለም። ዋናው ችግር ሣንመርጥ የቀረነውንና የውሳኔያችን አካል ባለመሆኑ ምክንያት ያልኖርነውን ህይወት መመኘታችን ነው።

የተውነው መንገድ የተሻለ፣ ቀለል ያለ፣ ደስታን የሚያጎናጽፍ ፣ ወይም የበለጠ ስኬታማ ሊያረገን ይችል እንደነበረ አርገን እናስብና ያን መንገድ መርጠነው ቢሆን ኖሮ አብሮት ሊመጡ ይችሉ የነበሩትን ችግሮች እንዘነጋለን።

ምርጫችን ምንም ይሁን ምን - ያን መንገድ ተከትዬ ቢሆንስ ኖሮ ምን ይከሰት ይሆን? የሚል ጥያቄ በውስጣችን መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ይህ አስተሳሰብ ግን መጥፎ ውሳኔ ወስነን ነበር ማለት ሳይሆን የተለመደ ሰውኛ ባሕሪ እያሳየን ነው።

ፍፁማዊ የሆነ ውሳኔ እወስናለሁ ብለን የማይሳካ እቅድ ይዘን ህይወታችንን ሙሉ ከምንባዝን እጃችን ላይ ባለው መረጃ ላይ ተንተርሰን መተግበር የምንችለውን ጥሩ ውሳኔ መወሰን ይመረጣል።

ሁሉም የህይወት መንገዶች መስዋዕትነት እንዳለባቸው በመረዳት የመረጥነውን መንገድ አጥብቀን ይዘን ውጤታማ ለመሆን መጣር ብልህነት ነው።

ደስተኛ ሰዎች በውሳኔዎቻቸው ላይ ጥያቄ የማያነሱቱ ሳይሆኑ የራሳየውን ህይወት ካልተጨበጠና ሊሆን ይችል ነበር ከሚሉት ነገር ጋር የማያወዳድሩት ናቸው።
ውስጣዊ ሰላም የሚመጣው ፍፁማዊ የሆነ ውሳኔን ወስኖ ከመገኘት ሳይሆን የመረጥነውን መንገድ ከልብ ተቀብለን መኖር ስንጀምር ነው።

ዶክተር ሲራክ ሀይሉ
ካይሮፕራኽተር
ከሚኔሶታ

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.