Logo
EBC
የሸገር ወንዞች ሲፈውሱ፡- ከብክለት ወደ ሕዝብ መዝናኛነት
********************

አዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያስመዘገበችው ግዙፍ የከተማ ገጽታ ለውጥ ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ ባሻገር የከተማዋን ነዋሪዎች አኗኗር፣ ማኅበራዊ መስተጋብርና የኢኮኖሚ አቅጣጫ የቀየረ ጥልቅ ስትራቴጂካዊ ሽግግር ነው።

ለረጅም ዘመናት አዲስ አበባ በከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ማደግ፣ በኮንክሪት ሕንጻዎች መበራከትና በአረንጓዴ ሥፍራዎች መመናመን ትታወቅ የነበረች ቢሆንም በቅርቡ የተከናወኑት የተቀናጁ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ግን ከተማዋን ወደ አዲስ የዕድገትና የውበት ምዕራፍ አሸጋግረዋታል።

ይህ ዘመናዊ ለውጥ በተለይም ቀደም ሲል የብክለት፣ የቸልተኝነትና የከተማዋ የጀርባ ገጽታ መገለጫ የነበሩትን የውሃ አካላትና ተፋሰሶች ወደ ሕያው፣ ማራኪና ሥነ-ምህዳራዊ ጠቀሜታ ወደላቸው የሕዝብ መጠቀሚያዎች በመለወጥ ረገድ ያተመዘገበው ስኬት የከተማዋን ታሪክና ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።

ይህ ዓይነቱ ትራንስፎርሜሽን የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ጥራት ከማሻሻሉም በላይ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ መድረኮች ያላትን የላቀ አቋምና የቱሪስት መዳረሻነት በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገው ይገኛል።

ለዚህም በዋና ማሳያነት የሚጠቀሰው ከእንጦጦ ጋራ ተነስቶ እስከ ቀበና የሚዘልቀው የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ነው። ይህ ሰፊ ኮሪደር ቀደም ሲል ለደህንነት አስጊና በቆሻሻ መጣያነት ያገለግል የነበረ አካባቢን ወደ ዘመናዊ የሕዝብ መዝናኛ፣ የእግር ጉዞ መንገዶችና የአረንጓዴ ልማት ማዕከልነት እንዴት መቀየር እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ታላቅ ስኬት ነው።

በእንጦጦ እና በቀበና ተፋሰስ መካከል በተገነቡት ዘመናዊ የሕዝብ መጠቀሚያ ሥፍራዎች ውስጥ የሚገኙት ውብ የእግር ጉዞ መስመሮች፣ የተፈጥሮን ሚዛን የጠበቁ የአትክልትና የዛፍ ዝርያዎች እንዲሁም ለዕረፍትና ለንባብ የተዘጋጁ ምቹ መቀመጫዎች ተፈጥሮንና ዘመናዊነትን በአንድ ጥላ ሥር ያቀናጁ ናቸው።

ነዋሪዎችና ጎብኚዎች ከከተማዋ የዕለት ተዕለት ጫጫታና ውጥረት ወጥተው ንጹህ አየር የሚተነፍሱበት አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነታቸውን የሚያድሱበት ሰላማዊ ምኅዳር ተፈጥሯል።

ይህ መሠረተ ልማት በከተማ ፕላን ውስጥ ለሰዎች ቅድሚያ የመስጠትን መርህ ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ወንዞች የከተማዋ የጀርባ አጥንትና የውበት መገለጫ መሆን እንደሚችሉ ያስመሰከረ አብነት ነው።

የዚህ የገጽታ መቀየር ዘላቂ ፋይዳ በዋናነት በሦስት ታላላቅ ዘርፎች ጎልቶ ይታያል። የመጀመሪያውና ግዙፉ ተጽዕኖ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የታየው አስደናቂ መነቃቃት ነው። አዲስ አበባ ቀደም ሲል የዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና የትራንዚት መንገደኞች ጊዜያዊ ማረፊያ ብቻ ሆና የምትታወቅበትን የቆየ ገጽታ በመቀየር አሁን ላይ ጎብኚዎች ቀናትን አሳልፈው የሚዝናኑባትና የሚጎበኟት እውነተኛ የመዳረሻ ከተማ እየሆነች ነው።

የወንዝ ዳርቻዎቹ ውበት፣ ማራኪ የውሃ ፏፏቴዎችና በምሽት በደማቅና ውብ መብራቶች የሚዋቡት ፓርኮች ለምሽት ቱሪዝም አዲስ በር ከፍተዋል። ይህም የፎቶግራፍ አፍቃሪዎችንና ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን የሚስቡ በርካታ ማራኪ ቦታዎችን በመፍጠር የከተማዋን ዓለም አቀፍ ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ገንብቶታል።

ሁለተኛው ከኢኮኖሚ ዕድገትና ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዘ ነው። በእነዚህ የተገነቡ የሕዝብ መጠቀሚያዎች ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት፣ ባህላዊ የምግብና የመጠጥ አቅራቢዎች እንዲሁም የዕደ-ጥበብ ውጤቶች መሸጫዎች ለበርካታ ዜጎች ዘላቂ የገቢ ምንጭና የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ይህ ሁኔታ የከተማዋን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ በማነቃቃት የቱሪዝም ኢኮኖሚው በቀጥታ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲደርስ አድርጓል።

ሶስተኛውና ትልቁ ስኬት የአካባቢ ጥበቃና የስነ-ምህዳር ሚዛንን ከመጠበቅ አንጻር የተመዘገበው ዘላቂ ውጤት ነው። ወንዞችን ከኢንዱስትሪና ከቤት ውስጥ ብክለት መታደግ መቻሉ፣ በዳርቻዎቻቸው ላይ የተተከሉ አረንጓዴ ተክሎችና ዛፎች የከተማዋን የካርቦን ልቀትን ለመቀነስና ብዝሃ ሕይወትን መልሶ ለማደስ ያላቸው ሚና ወደር የለውም።

በአጠቃላይ ሲታይ በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመዘገበው የወንዝ ዳርቻ ልማትና የውበት ስራ ከተማዋን ይበልጥ ለኑሮ ተስማሚ፣ ለዐይን ማራኪና በኢኮኖሚ ረገድ እራሷን የቻለች ማዕከል እያደረጋት ይገኛል።

ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ የልማት አካሄድ አዲስ አበባ በአፍሪካ አህጉር ያላትን ተወዳዳሪነት ይበልጥ የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ለቀጣይ ትውልድ የሚሻገር ታላቅ የታሪክና የውበት ዐሻራ ነው።

በበረከት ሽመልስ
#addisababa #riversidedevelopment #greenlegacy #tourismethiopia #ethiopianbroadcastingcorporation

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.