Logo
EBC
የቀይ ባሕር ጥሪ እና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ትንሳኤ
*****************

(የዕለቱ መልዕክት)

​ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶችና የኃያላን የሽኩቻ መድረክ በሆነው በአፍሪካ ቀንድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ህልውና እና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከቀይ ባህርና ከባህር በር ጥያቄ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው።

ተፈጥሮና መልክዓ-ምድራዊ እውነታዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት ቀይ ባህርና አባይ የዚች ታላቅ ሀገር የደም ስሮች ናቸው።

ከዚህ ተፈጥሯዊ ትስስር ባሻገር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር ህግ አንቀጽ 69 እና 125 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባሕር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም እና የመሸጋገሪያ አለም አቀፍ መብት እንዳላቸው በግልጽ ይደነግጋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ህጋዊና ተፈጥሯዊ መብቷን ለማስከበር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያከናወናቻቸው ስራዎች የሀገራችን መጻኢ ዕድል አዲስ አቅጣጫ ላይ ያስቀመጣት ሆነዋል።

​በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በባህርና ቀጠናዊ ተወዳዳሪነት ዙሪያ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ዋነኛውና ደማቅ ስኬት ሆኖ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል እንደገና መመስረቱና መዋቀሩ ነው።

ለሶስት አስርት ዓመታት ተዘንግቶ የነበረውን ይህንን ወሳኝ ዘርፍ በቁርጠኝነት ዳግም በማንሳት የባህር ኃይል አድሚራል በመሾም ተቋማዊ ኃይሏን በተግባር አጠናክራለች።

ይህ ስኬት በምኞት የተገነባ ሳይሆን አለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ አጋርነቶችን በመጠቀም፣ ለባህር ኃይሉ ዘመናዊ ስልጠናና ሁለንተናዊ የቴክኒክ ድጋፍ በማሰባሰብ የተመዘገበ ታላቅ ውጤት ነው።

ይህ ተቋማዊ ትንሳኤ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ኮሪደር ላይ ሊኖራት የሚገባውን ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ እና የተጠቃሚነት ፍላጎት በፅኑ መሠረት ላይ ያቆመ ኩነት ነው።

​የተከናወኑት እነዚህ ስራዎች የባህር በር ጉዳይን ከስሜታዊነት በራቀ፣ በጥንቃቄና በመርህ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እሳቤ መሆኑን ለአለም ማህበረሰብ ያሳዩ ናቸው።

10 በመቶ የሚሆነው የአለም ንግድ በሚያልፍበት፣ በዘይትና በከበሩ ማዕድናት በበለፀገው እና በቢሊዮኖች የሚቆጠር የንግድ እንቅስቃሴ በሚስተናገድበት በቀይ ባህር ቀጠና ውስጥ፣ ኢትዮጵያ የነበራትን የጥገኝነት መገለጫ በመቀየር የራሷን የባህር ኃይል መገንባቷ ወደፊት ለሚደረጉ የዲፕሎማሲ ድርድሮች ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

ይህ ስኬት የቀድሞ መሪዎች ስለ አባይ መብት ሲናገሩ "እኔ አቅም የለኝም ልጆቼ ይሰራሉ" እንዳሉት ሁሉ ዛሬ የተጣለው መሠረትም ትውልዱ የቀይ ባህርን መብት በሰላማዊ መንገድና በአለም አቀፍ ህግጋት መሠረት አስከብሮ እንዲረከብ የሚያስችል አርቆ አሳቢ እርምጃ ነው።

​ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተመዘገቡት ስኬቶች ኢትዮጵያ ጦር ሳትሰብቅ፣ የወንድማማች ሀገራትን ሉዓላዊነት ሳትደፍር፣ የራሷን ስትራቴጂካዊ ቦታ የምታስከብርበትን መዋቅር የፈጠሩ ናቸው። የባህር ኃይሉ መደራጀት ሀገራችን በአለም አቀፍ የባህር ህግ የተሰጧትን መብቶች በተግባር ለመተርጎም ያላትን ዝግጁነት ያረጋገጠ ሲሆን ለቀጣዩ ትውልድም ከስሜት ነጻ በሆነ መንገድ የተሰላ፣ የታመቀ አቅም እና ብሩህ የባህር በር ተስፋን የጫረ ታሪካዊ ስራ ነው።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.