Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ዛሬ ሐሙስ ባወጣው እና ዘ-ሐበሻ በተመለከተው ይፋዊ መግለጫ መሠረት፣ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ እናት የሆኑት ወይዘሮ አዳነሽ በርሀ በተወለዱ በ97 ዓመታቸው ጁን 22 ቀን 2026 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የዕረፍት ዜናቸውን ተከትሎም ሰኔ 24 ቀን 2026 ልጃቸው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶች እና ወዳጅ ዘመዶች በተገኙበት "ጸሎት" በተሰኘው የመቃብር ስፍራ ሥርዓተ ቀብራቸው በክብር ተፈጽሟል።

መግለጫው ላይ እንደተመለከትነው ከሆነ፣ ወይዘሮ አዳነሽ ከአባታቸው አቶ በርሀ ወልደሐዋርያት እና ከእናታቸው ወይዘሮ መድህን ስእሉ በ1929 በአስመራ ከተማ ተወለዱ። ለትምህርት በደረሱበት ወቅት በስኳላ ቪቶርዮ አስመራ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በወቅቱ በነበረው የህብረተሰብ ባህል መሠረት ገና የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ እያሉ ከአቶ አፈወርቂ አብርሃም ጋር ትዳር የመሰረቱ ሲሆን፣ ለአካለ መጠን እስኪደርሱ በወላጆቻቸው እንክብካቤ ስር ከቆዩ በኋላ የራሳቸውን ቤተሰብ ማስተዳደር ጀምረው በ15 ዓመታቸው የበኩር ልጃቸውን ወልደዋል።

በ42 ዓመታት የትዳር ዘመናቸው አስራ አራት ልጆችን ያፈሩት ወይዘሮ አዳነሽ፣ ዘጠኙን ልጆቻቸውን ለኤርትራ የነጻነት ትግል አበርክተዋል። ከእነዚህም መካከል ሁለቱ በትግሉ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ አንደኛው ደግሞ በ1966 በ20 ዓመቱ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ ትግሉን የተቀላቀለው እና በኋላም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የሆነው ኢሳይያስ አፈወርቂ ነው። ወይዘሮ አዳነሽ ታጋይ ልጆችን እና በተለይም በወቅቱ የትግሉ መሪ የነበሩትን የኢሳይያስ አፈወርቂን እናት በመሆናቸው ምክንያት በእሳቸው፣ በባለቤታቸው እና በቀሪ ቤተሰባቸው ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እና ጫና ደርሶባቸው ነበር።

በነበረው አስጨናቂ የፖለቲካ ድባብ ምክንያት በአስመራ ከተማ መኖር ባለመቻላቸው፣ በ1978 ስትራቴጂካዊ ማፈግፈግ በተደረገበት ወቅት በበረሃ አቋርጠው ጥቂት ልጆቻቸውን እና የልጅ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ አሜሪካ ተሰደዋል። ኤርትራ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ወይዘሮ አዳነሽ፣ በ1993 ባለቤታቸው አቶ አፈወርቂ አብርሃም ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩዋቸውም፣ ቀሪውን የህይወት ዘመናቸውን በልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው ተከበው አሳልፈዋል። መግለጫው በማከከልም ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.