Logo
Getu Temesgen
ለግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ አስተማማኝ የጤና ዋስትና የሆነው የበቆጂ ሆስፒታል

‎📌 የሕክምና ጥራትን ከመዝናኛ ጋር ያቆራኘው ሆስፒታል

‎#ethiopia | ​በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ደማቅ ስሟ በወርቅ ቀለም የተጻፈውና የአትሌቶቻችን መፍለቂያ ተብላ የምትታወቀው የበቆጂ ከተማ፣ በአሁኑ ወቅት በሩጫዋ ብቻ ሳይሆን በጤናው ዘርፍም እያሳየች ባለችው አስደናቂ ለውጥ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበች ትገኛለች።

‎በአካባቢው የሚገኘው የበቆጂ ሆስፒታል ካለፈበት የዕድገት ጉዞ አንስቶ አሁን ላይ እየሰጠ ያለው ሰፊና ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት፣ ከተማዋን በጤናው ዘርፍም የልማት ተምሳሌት አድርጓታል።

‎​ይህ ሆስፒታል በ2004 ዓ.ም. ተመስርቶ በ2007 ዓ.ም. መደበኛ ሥራውን ሲጀምር፣ በአካባቢው ለነበሩ 250 ሺህ ለሚጠጉ ነዋሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ነበር። ሆኖም ግን ተቋሙ በየጊዜው በሚያሳየው ተጨባጭ የሥራ መሻሻልና ውጤታማነት ምክንያት፣ በ2018 ዓ.ም. በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ በተደረገለት ግምገማ ደረጃው ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል እንዲያድግ ተደርጓል።

‎ይህ የደረጃ ዕድገት ሆስፒታሉ ቀደም ሲል ከነበረው የአገልግሎት አድማስ በላቀ መልኩ አቅሙን እንዲያሳድግና በአሁኑ ወቅት ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆን ሕዝብ ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና ድጋፍ እንዲያበረክት አስችሎታል።

‎​የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልፈታ አደም የሆስፒታሉን አጠቃላይ የአገልግሎት ጥራትና አሰራር አስመልክተው ሲናገሩ፣ ተቋሙ አሁን ላይ ከበቆጂ ከተማ ባለፈ በዙሪያው ለሚገኙ እንደ ሌሙ ቢልቢሎ፣ ዶዶላ፣ ሲርካ፣ ሀንቆሎ ዋቤና ገደብ ሀሳሳን የመሳሰሉ በርካታ የምዕራብ አርሲ ወረዳዎችን እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

‎እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ፣ ሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጡን ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ ሙሉ በሙሉ በሲሲቲቪ ካሜራ የሚደረግበት ሲሆን፣ ይህም በየክፍሉ የሚሰጡ ሕክምናዎችንና የኅብረተሰቡን ቅሬታዎች በቅርበት ለመከታተል ትልቅ እገዛ አድርጓል። ከተለመደው አሰራር በተለየ መልኩ፣ የሆስፒታሉ ሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች ወደ ተለያዩ የገጠር ጤና ጣቢያዎች በአካል ወርደው ሙያዊና የሕክምና ድጋፍ እንደሚሰጡ እንዲሁም ከአሰላ ሆስፒታል ጋር የቴሌ ሜዲሲን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ታካሚዎች ሳይንገላቱና ብዙ ወጪ ሳያወጡ ያሉበት ቦታ ሆነው የባለሙያ ምክር እንዲያገኙ እያደረጉ መሆኑን አቶ አብዱልፈታ በሰፊው አብራርተዋል።

‎​የበቆጂ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ብርሃኔ ነገሰ በበኩላቸው፣ ሆስፒታሉ እያከናወነ ያለውን ስር ነቀል የሪፎርም ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ አድንቀዋል። ከንቲባዋ እንዳሉት፣ ተቋሙ የመንግስትን የጤና ፖሊሲና አቅጣጫ በአግባቡ በመተግበር የውስጥ ገቢውን ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ ይህም መድኃኒቶችን ራሱን ችሎ በመግዛት ለማኅበረሰቡ በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርብ አስችሎታል። ከንቲባዋ አክለውም፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የመጡ የተለያዩ ብሔረሰቦች ስብጥር ያላቸው ሐኪሞች፣ ነርሶች፣ የጽዳትና የጥበቃ ሠራተኞች በመናበብና ሙሉ ጊዜያቸውን በመስጠት ሕዝባቸውን በቅንነት እያገለገሉ መሆኑን በኩራት ገልጸዋል።

‎​ይህ የሕክምና አገልግሎት ዘመናዊነትና ጥራት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ የተከናወነው ሁለተኛው ትልቅ ስኬት ደግሞ የአካባቢውን ገጽታ የመቀየር ሥራ ነው። ቀደም ሲል በተፈጥሮ ድንጋዮች ተሸፍኖ የነበረውን አስቸጋሪ መሬት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቭ መነሻ በማድረግ የሆስፒታሉ ማኔጅመንትና ሠራተኞች በጋራ በመረባረብ ወደ ማራኪ መዝናኛነት ቀይረውታል።

‎​ይህንን አስመልክቶ አቶ አብዱልፈታ አደም ሲያብራሩ፣ "አብዛኛው ኅብረተሰባችን ለመታከም ብቻ ሳይሆን ለመዝናናትም ጭምር ነው ወደ ሆስፒታላችን እየመጣ ያለው" ብለዋል። በግቢው ውስጥ ለአዋቂዎችና ለሕፃናት ተለይተው የተዘጋጁ ሙሉ ፓኬጅ ያላቸው መጫወቻና ማረፊያ ቦታዎች የተገነቡ ሲሆን፣ ይህም በተለይ ሕፃናት ወደ ሕክምና ተቋም ሲመጡ የሚሰማቸውን የ"መርፌ ፍርሃት " አስወግዶ በደስታ እንዲመጡ አድርጓቸዋል። ቦታው ቅዳሜና እሁድ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ማኅበረሰቡ ከቤተሰቡ ጋር የሚዝናናበት ቦታ መሆን ችሏል።

‎ወይዘሮ ብርሃኔ ነገሰም ይህንን አስደናቂ ለውጥ ሲያጠቃልሉ፣ የሰው እጅ ከሠራ የማይለውጠው ነገር እንደሌለ በተግባር የታየበትና ተቋሙ ከሕክምና መስጫነት ባለፈ የከተማዋ ውብ መዝናኛ እስከሚመስል ድረስ በላቀ ጥረት የተገነባ የኩራት ምንጭ መሆኑን በምስጋና መስክረዋል።

‎በጌትነት ተመስገን

‎Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)

‎#getutemesgen #getu #ጌጡ

‎#ethiopia #healthsector #bokojihospital #healthcarereform #oromiahealth


2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.