Logo
EBC
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እያነቃቃ ያለው አረንጓዴ ዐሻራ
*************

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ባለፈ የሀገርን የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) አቅም በአዲስ መልክ እየቀረጸው ይገኛል።

በተለይም በዘርፉ የተከናወኑ የመስኖ እና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የቡና እና የአቮካዶ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንድታመጣ ምክንያት ሆነዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአፈር እርጥበት ጥበቃ እና በሥነ ምህዳር መረጋጋት አማካኝነት የቡና ልማት አቅምን አሳድጓል።

ለበርካታ ዓመታት በዝናብ ጠባቂነት ላይ ተመስርቶ የቆየው የቡና ልማት፣ ከተፋሰስ ልማት በተገኘው የውኃ ሚዛን እና የአፈር ጥራት መሻሻል ምርታማነቱ በእጅጉ ጨምሯል።

ይህ የምርታማነት መጨመር ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት በማሳደግ በቡና ንግድ ታሪኳ ከፍተኛውን ገቢ እንድታገኝ አስችሏታል።

በሌላ በኩል መርሐ ግብሩ የፈጠረው ምቹ የአየር ንብረት እና የአፈር ሁኔታ አቮካዶን እንደ ዋና የንግድ ሰብል ለማልማት ዕድል ፈጥሯል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለአውሮፓ እና ለመካከለኛው ምሥራቅ ገበያዎች ጥራት ያለው አቮካዶ በማቅረብ ላይ ትገኛለች።

ይህም ለኢኮኖሚው አዳዲስ የገቢ ምንጮችን በመክፈት የንግድ ሚዛን መዛባትን ለመቀነስ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

እየተሻሻለ የመጣው የግብርና ምርቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት የመቀየር እና በከፍተኛ መጠን ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ጥንካሬን ፈጥሯል።

የቡና እና የአቮካዶ ምርት ዕድገት የሀገራችንን የኤክስፖርት ገቢ ከማሳደግ ባለፈ የአርሶ አደሩን ገቢ በመጨመር የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን አነቃቅቷል።

በጥቅሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ በኢኮኖሚ ጠንክራ እንድትወጣ እና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንድታስመዘግብ መሠረት እየጣለ ይገኛል።

በሃና ምንዳሁን
#ethiopia #greenlegacy #economy #export #coffee #avocado #ebc

18 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.