Logo
FBC
ሰላም፣ ደህና አደራችሁ?

ታሪክና መልክዓ ምድር ያቆራኛቸው የኢትዮጵያና የቀይ ባሕር ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ከቅርብ አሥርት ዓመታት ወዲህ ግን ይህ እውነታ ተቀይሮ ቆይቷል።

በታሪካዊ ስሕተቶችና በሴራ መንገዶች የባሕር በሯን ያጣችው ኢትዮጵያ ጉዳዩን ማንሳት እንኳን እንደ ነውር ወደሚቆጠርበት የስነ-ልቦና ስብራት ውስጥ ገብታ ነበር።

ይህ ሁኔታ ሀገሪቱ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እና ለደህንነት ስጋት እንድትጋለጥ አድርጓታል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የባሕር በር ጉዳይ ከነበረበት የመዘንጋት አዙሪት ወጥቶ የብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ አጀንዳ ወደ መሆን ተሸጋግሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሁለት ውሃዎች (የዓባይ ወንዝ እና የቀይ ባሕር) ፖሊሲን ይፋ በማድረግ ይህንን ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት አዳዲስና ቁርጠኛ እንቅስቃሴዎች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ይሁንታ እየተቸረው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር በር ጉዳይን የብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ ሀገራዊ አጀንዳ እንዲሆን በማድረግ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲቆሙ መንገድ ጠርገዋል።

የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የሚበይኑትን የዓባይ ወንዝ እና የቀይ ባሕር ጉዳይን በተመለከተ የሁለት ውሃዎች ፖሊሲን ይፋ አድርገው ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችውን የባሕር በር በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለማስመለስ የሚያስችል እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል።

ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተዋሳኝነቷን ስታጣ በሰነድ የተደገፈ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለመኖሩ ውሳኔው ሕጋዊ እንዳልሆነ እና ኢትዮጵያ በብዙዎች ርብርብ የባሕር በር ማጣቷን ያሳያል።

በባህር በር ጉዳይ መጠየቅ ነውርና ትክክል እንዳልሆነ የሚመለከት ትርክት በመፈጠር የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን ለመጋረድ ቢሞክርም አሁን ላይ በሰከነ መንገድ በውይይት የባሕር በር ማግኘት እንደሚቻል ግልጽ እየሆነ መጥቷል።

5 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የቀይ ባሕር ከ20 ሚሊየን የማይበልጥ ህዝብ ባላቸው ሀገራት መሸፈኑ ፍትሃዊ አለመሆን፥ ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ለዘለዓለሙ ተነጣጥለው መኖር እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው።

130 ሚሊየን ሕዝብ የያዘችው ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ድርሻ ሊኖራት ግድ በመሆኑ ብሔራዊ ጥቅሟንና ደህንነቷን ለማረጋገጥ የባህር በር ጥያቄዋ ምላሽ ማግኘት አለበት።

ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ጦርነት ሳይሆን ውይይትና ዲፕሎማሲ ቀዳሚው አማራጭ ሆኖ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ ከተደረጉ እንቅስቃሴዎች መካከል የአሰብ ወደብን ለማልማት በተደጋጋሚ ንግግር ቢደረግም ከኤርትራ መንግሥት በኩል ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነት የለም።

የባሕር በር ጉዳይ በውይይት እንዲሁም በገበያ ህግ ድርድር እልባት እንዲያገኝ አቋም ያላት ኢትዮጵያ፤ የባሕር በር የማግኘቷ ጉዳይ አይቀሬ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ማንም ፈለገም አልፈለገም ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት የሀገርን ኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የሚወስን ቁልፍ የብሔራዊ ጥቅምና የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ ለጥያቄው ምላሽ ማግኘት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የቤት ስራ አለባቸው።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.