Logo
YenetaTube
"ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉአላዊነት " በሚል መሪ ቃል ክልላዊ የኢትዮጵያ ታምርት ማጠቃለያ መርሐ ግብር ነገ በኮምቦልቻ ከተማ ይካሄዳል።

ኮምቦልቻ: ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ)

የአብክመ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢትዮጵያ ታምርት ክልላዊ የማጠቃለያ መድረክ ነገ ግንቦት 30/2018 ዓ.ም በኢንዱስትሪ መንደሯ ኮምቦልቻ ከተማ ያካሂዳል። የማጠቃለያ መርሐ ግብሩም "ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ መልዕክት ነው የሚካሄደው።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የነበሩ ችግሮችን እየፈታ መምጣቱን ገልጸዋል።

የማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ከመካሄዱ አስቀድሞ 159 የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄዎች በየደረጃው ሲካሄድ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ማምረት አለባት ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ማምረት የሕልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መኾኑን ነው የገለጹት። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአማራ ክልል በርካታ ትሩፋቶች እያመጣ ነው ብለዋል።

ንቅናቄው የክልሉን ጸጋዎች በማስተዋወቅ አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ እንዲመጡ ማድረጉን ተናግረዋል። በበጀት አመቱ ባለፉት ወራት 414 ቢሊዮን ብር ሀብት ያስመዘገቡ 3 ሺህ 518 ባለሀብቶች ወደ ክልሉ መጥተው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማውጣታቸውን አስታውቀዋል።

880 ባለሀብቶች ደግሞ ፕሮጄክቶችን አቅርበው ማስገምገማቸውን ገልጸዋል። 158 መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ ወደ ምርት መግባታቸውንም አንስተዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ አምራች እንዱስትሪው እንዲያድግ እያደረገ መኾኑን ነው የገለጹት።

በክልላዊ ማጠቃለያ መርሐ ግብሩ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኤክስፖ ምርቶቻቸውን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራቾች ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ እና ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በማጠቃለያ ኤክስፖው 145 አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚሳተፉም አንስተዋል።

በመርሐ ግብሩ በባለፉት ዓመታት ውጤታማ ለነበሩ አምራች ባለሀብቶች ዕውቅና እንደሚሰጥም ኃላፊዉ አመላክተዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎችም ከነገ ጀምሮ ወደ ኤክስፖው እየገቡ ምርቶችን እንዲጎበኙ እና በኤክስፖው ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት የሚድያ ማስተባበር ሥራ በተወዳጅ ሚድያ የተከናወነ ነው።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.