Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማእከላይ ኮሚቴ ከግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል ሲያካሂድ የቆየውን አስቸኳይ ስብሰባ ማጠናቀቁን አስመልክቶ ይፋዊ መግለጫ አውጥቷል።

ሕወሓት ባወጣው መግለጫ ላይ እንደሰፈረው በመቐለ ከተማ በተጠናቀቀው ጉባኤ ላይ ድርጅቱ ያለበትን ወቅታዊ ቁልፍ የውስጥ ችግሮች፣ ድክመቶች እና የቀጣይ የትግል አቅጣጫዎችን በዝርዝር ገምግሟል። ማእከላይ ኮሚቴው የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ ቀያቸው ለመመለስ እና የትግራይን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚደረገውን ትግል አጠናክሮ ለመቀጠል መወሰኑን በመግለጫው ጠቅሷል።

በዚህ ጥልቅ ግምገማ ድርጅቱ በውስጡ የነበሩ የአመለካከትና የአሰራር ጉድለቶችን ያለአንዳች ምህረት መመርመሩን የገለጸ ሲሆን፣ ህገ-ደንብን መሰረት በማድረግ በከፍተኛ አመራሮቹ ላይ ጠንከር ያሉ የዲስፕሊን እርምጃዎችን ወስዷል። በዚህም መሰረት በስራ ላይ የነበሩ ሁለት የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ አባላት እና አንድ የማእከላይ ኮሚቴ አባል ከባድ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ሌሎች በስራ ላይ የነበሩ አመራሮችም ከማእከላይ ኮሚቴ ተለይተው በትግል ሜዳ እንዲሰማሩና በሌሎች አዳዲስ አመራሮች እንዲተኩ ተደርጓል። ይህ እርምጃ ድርጅቱ የውስጥ አንድነቱን ለመጠበቅና የአመራር ብቃቱን ለማደስ የወሰደው ወሳኝ ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሆነ ተመልክቷል።

በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ እንደተመለከተው፣ ማእከላይ ኮሚቴው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር የካቢኔ አባላት እና የዞን አስተዳዳሪዎች አደረጃጀትን አስመልክቶ ሰፊ ውይይት አድርጓል። ድርጅቱ አዲስ የክልል ካቢኔ እንዲዋቀር እና የአመራር ሽግግር እንዲደረግ ፍላጎት እንዳለው ያመላከተ ሲሆን፣ ይህንኑ የአመራር ለውጥ የትግራይ ምስረታ ምክር ቤት እንዲመለከተው በይፋ መምራቱን አስታውቋል። ህወሓት በምርጫ ከፍተኛ ድምፅ ያገኘና ያሸነፈ ድርጅት በመሆኑ በክልሉ አስተዳደር ውስጥ ያለውን የመሪነት ሚና በህጋዊ አሰራር ለማስፈጸም እንደሚንቀሳቀስ በመግለጽ፣ አዲሱ መዋቅር የህዝቡን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ እንደሚሆን አረጋግጧል።

4 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.