Logo
EBC
የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን የአምራች ዘርፉን አቅም ለማሳደግ ትልቅ መሠረት እየጣሉ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን
************

እያደገ በመጣው የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ሚና በዋናነት ተጠቃሽ ነው።

ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ሁሉንም ዓይነት ኢንቨስትመንት ተቀብለው ማስተናገድ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ባለሃብቶችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።

እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይም ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

አሁን ባለው ሁኔታ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ምርቶቻቸውን በዋናነት ለዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ ይበረታታሉ።

በዚሁ መሠረት እንደ ጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ያሉ ምርቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ በማምጣት ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከኢኮኖሚ ምንጭነታቸው ባሻገር ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ባለሙያዎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን በተግባር አሳይተዋል።

በፓርኮቹ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሀገር ውስጥ የሰው ኃይልን በስፋት የሚጠቀሙ በመሆናቸው፣ ወጣቱ ትውልድ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምንና የላቀ የኢንዱስትሪ አመራር ክህሎትን በቀጥታ እንዲቀስም ምቹ መድረክ ፈጥረውለታል።

ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን የአምራች ዘርፉን ሀገራዊ አቅም ለማሳደግ ትልቅ መሠረት እየጣለ ይገኛል።

ትናንት በይፋ የተመረቀው የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክም የኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ለዓለም ይበልጥ ተደራሽ የሚያደርግ ነው።

ከተመሠረተ 11 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር በመላው ሀገራችን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ 14 ልዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ በማስተዳደር ላይ ይገኛል።

በሔዋን ጌታቸው
#ethiopia #manufacturing #industrialparks #specialeconomiczones #ebc

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.