Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በደቡባዊ ሊባኖስ በዛሬው ዕለት ዕለት በተፈጸመ የእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ባለስልጣናት ሲያስታውቁ፤ በበኩሏ እስራኤል ሄዝቦላህ ባስወነጨፈው ፈንጂ የጫነ ድሮን ሶስት ወታደሮቿ መቁሰላቸውን አረጋግጣለች። ባለፈው ኤፕሪል 16 በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታውጆ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት በአብዛኛው መፍረሱን የሚያሳየው ይህ የቅዳሜው ግጭት፣ ሁለቱ ኃይሎች ዳግም ወደ ለየለት ጦርነት ሊያመሩ እንደሚችሉ ስጋት ፈጥሯል።

ዛሬ ሄዝቦላህ በርካታ ፈንጂ የጫኑ ድሮኖችን እና ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ያስወነጨፈ ሲሆን፣ ከእነዚህም አንዱ ከሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ በማረፍ አንድ የእስራኤል ተጠባባቂ ወታደርን በከባድ እንዲሁም አንድ መኮንን እና ሌላ ወታደርን በመጠኑ ማቁሰሉን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ገልጿል። በአጻፋው የእስራኤል ጦር፣ ታይር ዴባ እና ማሩብን ጨምሮ ለዘጠኝ የደቡብ ሊባኖስ መንደሮች ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ፣ በሄዝቦላህ መሰረተ ልማቶች ላይ ሰፊ የአየር ጥቃቶችን አድርሷል።

ይሁን እንጂ የሊባኖስ መገናኛ ብዙሃን እና የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቁት፣ ምንም ዓይነት የማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ ባልተሰጠባቸው አካባቢዎች ጭምር በተፈጸሙ ጥቃቶች ንጹሃን ህይወታቸውን አጥተዋል። በናባቲዬ አካባቢ በሞተር ሳይክል ላይ ሲጓዙ በነበሩ አንድ ሶርያዊ አባት እና የ12 ዓመት ሴት ልጁ ላይ በተፈጸመ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት ሁለቱም ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በሳክሳኪዬ ከተማ በተደረገ ሌላ ጥቃት ደግሞ አንዲት ህጻንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከቤሩት በስተደቡብ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሳዲያት በተባለች ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ አውራ ጎዳና ላይ ሁለት ተሽከርካሪዎች በእስራኤል መመታታቸው ተዘግቧል።

የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ባለፈው አንድ ቀን ውስጥ ብቻ በደቡብ ሊባኖስ የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን፣ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን እና ሄዝቦላህ ለጥቃት የሚጠቀምባቸውን ህንጻዎች ጨምሮ ከ85 በላይ ኢላማዎችን መምታቱን አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በምስራቃዊ ቤቃ ሸለቆ የሚገኝ የሄዝቦላህ የመሬት ውስጥ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ጣቢያን ማውደሙን አክሎ ገልጿል። የሄዝቦላህን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት ተከትሎ ኃይለኛ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን የገለጸው የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ፣ ንጹሃንን የመጉዳት አላማ እንደሌላቸው ቢናገሩም በምድር ላይ ያለው እውነታ ግን የሲቪሎች እልቂት አሁንም አለመቆሙን እያሳየ ይገኛል።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.