Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ኢንዴፕዝ ኒውስ የተሰኘው ድረ ገፅ ላይ ዛሬ የቀረበውን ይህንን ጥናት ያከናወኑት ዳንኤል ተስፋ፣ ስሂም ማሻ፣ ጆሊ ስቶከርና መሪያም ቫን ሬሰን የተሰኙ ጋዜጠኞች ሲሆኑ ጉዳዩን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች እንደሚገልፁት ይህንን ጥናት ያከናወኑት ከማርች 9 ቀን እስከ ኤፕሪል 11 ባሉት ቀናት ነው፡፡ በጥናታቸው ከማእከላዊ ትግራይ ዞን አድዋን፣ ኢንትጮን፣ እድጋ አርቢናና አክሱምን ማካለላቸውን፣ ከምስራቅ ትግራይ ዞን ሀውዜን ከተማ መግባታቸውንና በደቡባዊ ዞን ደግሞ ነቅሰኝ ወረዳንና ከሰሜን ምእራብ ዞን ሽሬ መሄዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በማእከላዊ ትግራይ ዞን እዳጋ አርቢ ወረዳ የሚገኙት አንድ አባት ለዜና አውታሩ በሰጡት መግለጫ የህወሀት ካድሬዎች የግዳጅ ምልመላ ለማድረግ ወደአካባቢያው መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሲናገሩም ‹‹ማህበረሰቡን ለመቀስቀስ የህወሀት ካድሬዎች መጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን ልጆቻችንን ለጦርነት አንልክም ብለን ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርገናል›› ብለዋል፡፡ እኚህ አባት ጨምረው እንደገለፁት ልጆቻቸውን እንዲያዋጡ ለመቀስቀስ የተጠራው ስብሰባ በተቃውሞ ከተበተነ በኋላ የህወሀት ካድሬዎች ፖሊስና ታጣቂ ሀይል አሰማርተው እድሜያቸው ከ15 አመት በላይ የሆኑትን መዝግበዋል፡፡ እሳቸው ግን ‹‹ይሰሩኝ እንጂ ከዚህ በኋላ ልጆቼን ለጦርነት አልሰጥም›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የ17 እና የ15 አመት እድሜ ያላቸው እኚህ አባት ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ማስቀረት ባይችሉም በትምህርት ቤቶች ውስጥ የግዳጅ ምልመላ መኖሩ ስጋት እንዳሳደረባቸው አስታውቀዋል፡፡ በአህፈሮም ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ አረፈ ወልዳይ በበኩላቸው ‹‹እድሜያቸው ከ15 አመት በላይ የሆኑትን ልጆች መዝግበው ሄደዋል፡፡ እየተመለከትን ያለነው የጦርነት ምልክት ነው›› ያሉ ሲሆን የወረዳው ማህበረሰብ በግዳጅ እህል፣ ጥሬ ገንዘብና ምግብ እንዲያዋጣ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ጨምረውም ‹‹እያንዳንዱ ነዋሪ 25 ኪሎ እህል፣ 500 ብር፣ ምስርና እንቁላል እንዲያቀርብ ትእዛዝ ተሰጥቶታል፡፡ በትግራይ ጦርነት ወቅት ለሞቱት ልጆቻችን እያዘንን እንዴት ሌላ ዙር ጦርነት ልንቋቋም እንችላለን?›› የሚል ጥያቄም አንስተዋል፡፡ አቅም ያላቸው የወረዳው ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ወደአዲስ አበባ መላካቸውን ገልፀውም እሳቸው ግን ይህን ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ እንደሌላቸው አስረድቷል፡፡ በአክሱም የሚገኙት የቀድሞው የቲዲኤፍ አባል አቶ መስፍን ሀደራ በበኩላቸው የተሰናበቱ ታጣቂዎች በስልታዊ ዘዴ የመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አቶ መስፍን ጦርነቱ እንዳበቃ በዲዲአር ከተሰናበቱት መካከል አንዱ ቢሆኑም ‹‹የቀድሞ ወታደራዊ ክፍሌ አግኝቶ አናግሮኛል፡፡ ሌሎች እንደኔ የተሰናበቱም የስልክ ጥሪ ደርሷቸዋል›› ብለዋል፡፡ እንደገለፁትም ይህ ጥሪ የሚደረገው በማማለልና በማስፈራራትም ጭምር ነው፡፡

ሲናገሩም ‹‹ወደጦር ሀይሉ ለሚመለሱ መሬት እንደሚሰጡና የስራ እድል እንደሚፈጥሩ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ደግሞ ከሀዲ የሚል ስም እየሰጧቸው ነው›› ያሉት አቶ መስፍን የቀድሞ የቲዲኤፍ አባላት ጋር ወታደራዊ አዛዦችና የህክምና ባለሙያዎች እየተላኩ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ ዘገባው እንዳለው በደቡባዊ ዞን ነቅሴጌ ወረዳ የቀድሞ የቲዲኤፍ አባላት ወደነበሩበት ወታደራዊ ክፍሎች እንዲቀላቀሉ የሚጠይቅ ማስታወቂያ ተለጥፏል፡፡ ይህ ማስታወቂያም ‹‹በትግራይ ህዝብ ላይ የታወጀውን የጄኖሳይድ ጦርነት ተቃውማችሁ የታገላችሁ በሙሉ›› በሚል የሚጀምር ሲሆን ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ እንዲመለሱ የሚገልፅ መሆኑን አሳይቷል፡፡ እንዲህ አይነት ማስታወቂያዎችን በሌሎች ወረዳዎች መመልከቱንም አስረድቷል፡፡ የትግራይ ማእከላዊ ዞን የህወሀት ፅህፈት ቤት ለአድዋ ወረዳ ትምህርት ቢሮ በፃፈው ደብዳቤ ደግሞ ‹‹የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደወታደራዊ ክፍሎቻቸው እንደሚመለሱ› የሚል ትእዛዝ መያዙን ገልጿል፡፡

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.