Logo
YenetaTube
በስኬት ተጠናቋል!!

የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ ትላንት ማርች 21 (መጋቢት 12/2018 ዓ.ም) በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ማርዮት ሆቴል በተከናወነው የማጠቃለያ ገቢ ማሰባሰቢያ (ፈንድ ሬይዚንግ) መርሐግብር 350 ሺ ዶላር በማግኘት ስኬት መጠናቀቁን አቶ ብርሃን ተድላ የድርጅቱ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ ገለጹ።

የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ወጣት አዶናይ ብርሃነ አስተባባሪነት የልብ ሕሙማን ሕጻናትን ለማሳከም የሚውል የገንዘብ ማሰባሰብ መርሐግብር ለአንድ ሳምንት ያህል ሲከናወን ቆይቶ በትላንትናው እለት የኢትዮጵያውያን ደግነትና ፍቅር ጎልቶ በታየበት መድረክ በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በዚህ መሰረት በቀጥታ በባንክ ገቢ የተደረገ 110 ሺ ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ቀሪው ቃል የተገባና በአጭር ጊዜያት የሚሰበሰብ መሆኑን አቶ ብርሃን ጠቅሰው በኢትዮጵያውያን ወገኖች ርብርብ መደሰታቸውን ገልፀዋል።

በአሜሪካ ሀገር የሚገኙ የድርጅቱ የቦርድ አመራር አባላት ያሳለፉትን ውሳኔ መሰረት አድርገው አቶ ብርሃን እንደተናገሩት በተገኘው ገንዘብ ከዚህ ቀደም ባደረግነው የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት ከኢትዮጵያ ልብ ማኀበር ጋር በመነጋገር እንዲሁም የልብ ቀዶ ጥገና ከሚሰሩ የመንግስት ሆስፒታሎች እና የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀትና አስፈላጊውን የሕክምና ግብዐቶችን በማሟላት ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ
ሕክምና ለማግኘት በወረፋ ላይ ለሚገኙ 120 ሕጻናት የልብ ቀዶ ጥገና ለማከናወን እቅድ ተይዟል።

በተጨማሪም የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ በደረሰው ስምምነት መሰረት ኤኘሪል 24
መሰረታቸውን በጣሊያን ያደረጉት 3 ድርጅቶች ማለትም Una per Voce Padre Pio ፣ CCPM እና REBEL Hert'sን የተውጣጡ ባለሙያዎች አማካይነት 50 ተጨማሪ ሕጻናት በመንግሥት ሆስፒታል እና በኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን አብስረው ዝርዝር መረጃው በወቅቱ እንደሚገለፅ ጠቅሰዋል። ይኸም ክንውን በአጠቃላይ በወራት ጊዜያት ውስጥ ሕክምና የሚያገኙ ሕጻናትን ቁጥር 170 ያደርሰዋል።

የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ የታካሚዎችን እንግልት ለመቀነስ በማሰብ በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአራት የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ የልብ ቀዶ ጥገና ማእከላትን ለማቋቋም አቅዶ እየሰራበት እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል።

አቶ ብርሃን እንደተናገሩት በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የልብ ቀዶ ጥገና በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን አንድ የባለሙያዎች ቡድን እንደሚቋቋም ጠቁመው ኢትዮጵያውያን የልብ ቀዶ ጥገና ባለሙያዎች ቡድኑን ተቀላቅለው ለዚህ ታላቅ ተግባር ሙያዊና ወገናዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በገንዘብ ማሰባሰብ መርሐግብሩ የልብ ሕሙማን ሕጻናት እንዲታከሙ በቋሚነት ለማገዝ 150 ቋሚ አባላት መመዝገባቸውን የተናገሩት አቶ ብርሃን ይኸን ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ 500 ለማድረስና የሚታከሙ ሕፃናት ቁጥርንም ለማሳደግ እንዲረዳ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በቋሚ አባልነት እንዲመዘገቡ አቶ ብርሃን ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር እንዲሳካ የድርጅቱ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ወጣት አዶናይ ብርሃነ እና አስተባባሪዋ ወ/ሮ ሀና ክብሩ፣ ባለቤቷ ሳሚ ላደረጉት የላቀ አስተዋፅኦ በትላንትናው መርሐግብር ላይ የተዘጋጀላቸውን የዋንጫ ሽልማት ከመቀበላቸው በተጨማሪ ሌሎች የመርሐግብሩ አስተባባሪዎች የምስጋና የምስክር ወረቀት በክብር ተሰጥቷል።

በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ላይ በአካል ለመገኘት ከካልፎርኒያ፣ ከሲያትል፣ ከኒውዮርክ፣ ከቴክሳስና ከመሳሰሉት ግዛቶች ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በዋሽንግተን ዲሲ መገኘታቸውን አቶ ብርሃን አስታውሰው በዝግጅቱ ላይ 150 ያህል ተሳታፊዎች እንዲሁም በክብር እንግድነት የዋሽንግተን ዲሲ እጩ ከንቲባ ሚስተር ኬኒየን ማክደፊ፣
ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል፤ የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣
ሊቀ ማዕምራን ፕሮፌሰር ዘበነ ለማ
የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው አገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መገኘታቸውንና ለመርሐግብሩ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል።

በተጨማሪም በአሜሪካን፣ በካናዳ እና በሀገር ቤት የሚገኙ የሶሻል ሚድያ አጋሮች ላደረጉት የማይተካና የላቀ አስተዋጵኦ አቶ ብርሃን ተድላ፤ የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ አመስግነዋል። አብዛኛዎቹ የሶሻል ሚዲያ አጋሮች በቀጣይም የድርጅቱን ዓላማ ደግፎ ለመሥራት ቃል ገብተዋል።

እንዲሁም ደግሞ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኃላፊነታቸውን የተወጡ የድርጅቱ የቦርድ አመራር አባላት፤ ዝግጅቱን ስፖንሰር በማድረግ የላቀ እገዛ ያደረጉ ተቋማት፤ ድጋፍ በሚፈልጉት የልብ ሕሙማን ሕጻናት ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.