Logo
FastMereja
ኢትዮ ሆም ኤክስፖ 2026

በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ከመጋቢት 23 እስከ 25 የሚካሄደው ሆም ኤክስፖ 2026 ልዩ እና የመጀመሪያ የሚያደርገው ዋና ዓላማ በዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩ የዳያስፖራ ማህበረሰቡ አስተማማኝ በሆነ መንገድ የቤት ባለቤት እንዲሆን ለማስቻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱ ነው።

በእንግሊዝ አገር የሚካሄደውን መድረክ በትብብር ካዘጋጁት ባለድርሻ አካላት መካከል አንዱ የሆኑት የኤድማር ቬንቸር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋሲካ አብዛ፤ ኢትዮ ሆም ኤክስፖ 2026 የሚዘጋጅበት ለዳያስፖራ ማህበረሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ልዩ ግብ የሰነቀ መሆኑን ይናገራሉ።
እንደ እርሳቸው አነጋገር ይህ በእንግሊዝ አገር የሚካሄድ ኤክስፖ የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎችን፣የፋይናንስ ተቋማትን፣ፖሊሲ አውጭዎችን ፣ተግባሪዎችንና አስፈፃሚዎችን ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር የማገናኘት ግብ አለው።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሪል ስቴት አልሚዎች የበለጠ መተማመን እንዲኖረው ለማስቻል በማቀድ በተቀመጡ መመዘኛዎች እና የማጣራት ሥራ ከአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ሂደቱንም በተገልጋዩ ማህበረሰብ ዘንድ መተማመን እንዲፈጥር ለማስቻል ቀርቦ ማወያየት እና ግንዛቤ ማስጨበጡ መሠረታዊ መሆኑን አቶ ፋሲካ ያስረዳሉ። ይህንኑ ለማሳካትም የፓናል ውይይት ለማካሄድ ዕቅድ መያዙን ገልፀዋል።

ይህ የዳያስፖራ ማህበረሰቡ በሀገሩ የቤት ባለቤት የመሆን ህልሙን እውን ከማድረግ እና የሪል ስቴት ዘርፉን ከማንቀሳቀስ አንፃር ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ በሌሎች አገራትም ለማስፋፋት የሚሠሩ መሆኑን ገልፀዋል።

" .....ሪል ስቴት አልሚ ድርጅቶች ፣ ወደ እንግሊዝ አገር በመምጣት ለዳያስፖራ ማህበረሰቡ አገልግሎታቸውን ብሎም ድርጅታቸውን የሚያስተዋውቁበት ዕድል ፈጥረናል። በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በተቀመጡ መመዘኛዎች ተጣርተው የሚመጡ በመሆናቸው የሚያቀርቡት አገልግሎት ታማኝ እንዲሆን ያስችላል። በሚካሄደውም ፓናል ላይ ያሉ ችግሮች ምንድናቸው? ገዥው እንዴት ተጠቃሚ መሆን ይችላል? የሚለውን እያነሳን እናወያያለን። ኢትዮ ሆም ኤክስፖ በዚህ መልክ ሊካሄድ ታስቧል።" ሲሉ አቶ ፋሲካ ተናግረዋል።

የሆም ኤክስፖ 2026 ዋና አዘጋጅ በለንደን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ ሲሆን ኤድማር ቬንቸር ኤክስፖውን ያስተባብራል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የሪል ስቴት አልሚዎችን እና የዳያስፖራውን ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ድጋፍ በመስጠት ያዘጋጃሉ።

አቶ ፋሲካ "...ኤክስፖው ከሜይ 23 -ሜይ 25 ይካሄዳል።ሜይ 23 የፓናል ውይይት ሲደረግ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት የቤት ኤክስፖ ዕውን ይሆናል ።እነዚህ ቀናት ገዢው ከፋይናንስ ተቋማትና ከአልሚው ጋር የሚገናኝባቸው እና ውይይት የሚያደርግባቸው ቀናት ሆነው ይውላሉ። አጠቃላይ የሪል ስቴት አልሚዎቹ 30 የሚጠጉ ሲሆኑ ሁሉም ስለራሳቸው የሚያስተዋውቁበት አጋጣሚ የተፈጠረላቸው ስለሆነ በዚህ ዕድል እንደሚጠቀሙም ተስፋ እናደርጋለን " ብለዋል።

ይህንን መርሀ- ግብር ዕውን ለማድረግ ኤድማር ቬንቸር በማርች 30 2026 ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ሲሆን በዚህ መርሀ ግብር ላይም ከዳያስፖራው ኤጀንሲ፣ ከቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ፣ከባንኮችና ከሪል ስቴት አልሚዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።እንደ ኤድማር ቬንቸር የሥራ ኃላፊዎች ከሆነ ከመግለጫው በኃላ ሁሉን አቀፍ የሆነ የፕሮሞሽን ሥራ ይከናወናል። የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በሚገኝባቸው የዕምነት ተቋማት፣የንግድ ማዕከላት በመድረስ ስለሆም ኤክስፖው በቂ መረጃ እንዲገኝ የተቻለንን እናደርጋለን ሲሉ የኤድማር ቬንቸር የሥራ ኃላፊ አቶ ፋሲካ አፅንዖት ሰጥተው ያስረዳሉ።

በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ ሚድያው ሰፋ ተደራሽነት ያለው በመሆኑ እነርሱን በመጠቀም መረጃውን ለማሠራጨት እንደሚሞከር ተገልጿል።

አቶ ፋሲካ የበለጠ ሀሣባቸውን ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ "... እኛ በማህበራዊ ሚድያ ብቻ አንወሰንም። ተፅዕኖ ፈጣሪ የማህበረሰብ መሪዎች ፣ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመድረስ የማስተዋወቅ ሥራችንን አጠናክረን ቀጥለናል።መርሀ -ግብሩ የሚካሄድባቸውንም ስፍራዎች ከወዲሁ ይዘናል። ተሳታፊዎችን መመዝገብ ፣የጉዞ ሁኔታቸውን ማመቻቸት፣ እንዲህ ያሉ ዋና ዋና ቅድመ- ሁኔታዎችን አጠናቀን ጨርሰናል" ሲሉ አቶ ፋሲካ ይናገራሉ።

ኤድማር ቬንቸር ይህ ሥራ አንድ ተብሎ ከመጀመሩ አስቀድሞ በእንግሊዝ የተወሰነ ጥናት አድርጎ ነበር። ሁሉም በሚባል መልኩ አገሩ ላይ ቤት መገንባት ይፈልጋል። የጡረታ ዘመኑን አገሩ ላይ ማሳለፍ ይመርጣል። ወጣቱም ቢሆን አገሩ ላይ ቤት ገዝቶ ጥሩ የቢዝነስ አማራጭ ይሆንለታል።

የኤድማር ሰዎች ባጠኑት መሠረት በሁሉም የእድሜ፣የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ቤት የመግዛት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። በቅርበት ሆኖ የሚያስረዳቸው ከተገኘ ደግም ቤት የማይገዙበት አንዳች ምክንያት አይኖርም ሲሉ ጥናታቸውን አፅንኦት ሰጥተው ያቀርባሉ።

ይህ ኤክስፖ ለአገሪቱም የውጭ ምንዛሪ በማስገባት በኩልና የንግድ እንቅስቃሴውን በማሳደግ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ይታመናል።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.