Logo
FastMereja
የአማራ ባንክ በፋይናንስ ዘርፉ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

አማራ ባንክ አሁናዊ ቁመናው በፋይናንስ የተረጋጋ፣ ጤናማ አሰራር የዘረጋና በረጅም ጊዜ እድገት ላይ አተኩሮ እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን እናረጋግጣለን። ባንኩ ራሱን ለማጠናከርና ለኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እድገት ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ ለማበርከት ከተቆጣጣሪዎች፣ ባለአክሲዮኖችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መስራቱን ይቀጥላል።

የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንቱ በጋራ የባለአክሲዮኖችን ሀብት መጠበቅ፣የተቀማጭ ገንዘብ ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የህግና የቁጥጥር መመሪያዎችን መከተል፣ የተቋማዊ አስተዳደርን ማጠናከርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት የበኩሉን ድጋፍ መስጠት ተግባራትን በመፈፀም ግልጸኝነትና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የባንኩን ቀጣይነት ያለዉ እድገት ለማስቀጠል የማይናወጥ ቁርጠኝነታቸውን ያረጋግጣሉ።

ደንበኞቻችን፣ ባለአክሲዮኖቻችን፣ ሰራተኞቻችን፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና ባለድርሻ አካላት ለአማራ ባንክ ስለሚያሳዩት ቀጣይነት ያለው እምነትና ድጋፍ ምስጋና ያቀርባል።

የአማራ ባንክ ይህን ፕሬስ ሪሊዝ ያዘጋጀው የባንካችንን አሁናዊ ሁኔታ ባለአክሲዮኖቹ፣ ደንበኞቹና ህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲረዱት ለማድረግና በተመሳሳይ በባንኩ ላይ የተከፈተው የሚዲያ ዘመቻ ሆን ተብሎ በባንኩ ላይ ጫና ለማሳደርና መደበኛ የባንክ አገልግሎቱን በአግባቡ እንዳይሰጥ ለማወክ እንደሆነ ለማሳወቅ ነዉ፡፡

ሪፖርተር የአማራ ባንክን አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ውስጥ ያካተታቸው መረጃዎች በተለይ ህዝቡን ለማሳሳት የቀረቡ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉን ማናቸዉንም የባንኩን የስራ ኃላፊዎች አስተያየት ያላካተተ፣ በአብዛኛው በስም ያልተጠቀሱ ምንጮችን የተጠቀመ፣ ሀሰተኛና ባልተረጋገጡ መረጃዎች እና ሆን ተብለው የባንኩን ስም ለማበላሸት በማሰብ ለራስ ፍላጎትና ዓላማ በተመረጡ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ዘገባን ለህዝብ ማጋራቱ ተገቢነት ያለዉ ሆኖ አላገኘነዉም፡፡

ጋዜጣዉ እንደ ባንክ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቷል፤ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ለህትመት አብቅቷል። እንደ አንድ በቅርብ ዘርፉን እንደተቀላቀለ ባንክ ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሷል።

ባንኮች በደንበኞች፣ በአክሲዮን ባለቤቶች እና በህዝብ እምነት ላይ የተመሰረቱ ስለሆኑ እንዲህ ዓይነት ሀሰተኛ ዘገባ ያልተፈለገ ግርግርና መረበሽን ሊፈጥር ይችላል።

ይሁንና አማራ ባንክ ባለአክሲዮኖቹ፣ ደንበኞቹ፣ ተጠቃሚዎቹና ባለድርሻ አካላት ባንኩ የሚገኝበትን አሁናዊ እውነታ እንዲረዱት ይፈልጋል፡፡ ባንኩ በጠንካራና የተረጋጋ የፋይናንስ አቋም ላይ ሆኖ እየሰራ እንደሆነ፣ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መመሪያዎችን መሰረት አድርገዉ እየተፈፀሙ እንደሆነ፣ ከሚዲያ ተቋማትም ጋር ቢሆን በግልጽነትና መርህን ተከትሎ በአግባቡ እየሰራ እንደሆነ እና የባንኩን ባለአክሲዮኖችን፣ ደንበኞቹንና ባለድርሻ አካላትን መብትና ጥቅም ባስከበረ አግባብ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ በድጋሚ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

አማራ ባንክ አ.ማ
ከባንክ ባሻገር!
አዲስ አበባ፣ኢትዮጵያ

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.