Logo
SeledaPost
መደበኛ ፓስፖርት ለሚፈልግ አመልካች፤ 50 ሺህ ብር በመክፈል “በቤት ለቤት ልዩ አገልግሎት” በሁለት ቀናት ውስጥ እንዲያገኝ የሚያስችል ደንብ በስራ ላይ ዋለ።

ደንቡ ለ10 ዓመታት የሚያገለግል የኢትዮጵያን “ወርቃማ ቪዛ” (Golden Visa) በ10 ሺህ ዶላር ክፍያ ማግኘት የሚቻልበትን አሰራርም በውስጡ አካትቷል።

ይህንን አዲስ አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገው፤ ከየካቲት 17፤ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በስራ ላይ የዋለው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የክፍያ ደንብ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዚህ ደንብ ላይ ውይይት አካሄዶ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ የወሰነው፤ ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነበር።

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ተቋም ለሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች የክፍያ ተመኖችን የሚዘረዝረው ይህ ደንብ፤ በአራት ዓመት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ እንዲሻሻል የተደረገ ነው።

የአሁኑ ማሻሻያ የተደረገው፤ በሐምሌ 2016 ዓ.ም. የወጣው ደንብ አተገባበር ላይ “የታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል” እንዲሁም “የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲያፈሩ የተደነገገውን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ” እንዲያስችል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው አዲሱ ደንብ ላይ፤ በሁለት እና በአምስት ቀናት ውስጥ ለሚሰጡ የመደበኛ ፓስፖርት አገልግሎቶች ሲጠየቅ የነበረው ከ5 ሺህ እስከ 25 ሺህ ብር የሚደርስ ክፍያ ሳይለወጥ ቀጥሏል። ሆኖም መደበኛ ፓስፖርትን “በልዩ አገልግሎት” ለማግኘት የሚፈልጉ ተገልጋዮች ከ40 እስከ 50 ሺህ ብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው በደንቡ ላይ ሰፍሯል።

seledadotio
seledadotio
3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.